አያቴ


በልጅ አዕምሮዬ ውስጥ ትልቅ የትዝታ ስዕል ስለውብኝ ካለፉት ሰዎች መካከል አልፎ አልፎ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ከማጣጥማቸው መልካም ትዝታዎቼ ውስጥ የእናቴ አባት አንዱ ነው፡፡
ከተረቶቹና ምሳሌዎቹ፣ከማያልቁት ወጎቹ፣ከምንም በላይ ደግሞ ተረብ አዋቂነቱ ብዙ የሕይወት ፍልስፍናዎችን አስዘርፎኛል፡፡ ከምንም በላይ የምቀናበት በሰባዎቹ መጨረሻ ሆኖ የነበረው ጤነኝነትና ጥንካሬ፣ የሥራ ፍቅር ከወዲያኛው ዘመን ጠንካራና ጤናማ ሕይወትን በደግ ዘመን ካጣጣሙት የአቢሲኒያ ልጆች ሕይወትን ቁልጭ አድርጎ ያሳየኝ ሕያው መስታወት ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ስንቶቻችሁ ሰለ አያቶቻቹ ጥልቅ የሆነ ጥዑም ትዝታ እንዳላችሁ ባላውቅም እኔ ግን ከተማርኳቸው ብዙ ቁም ነገሮች ጥቂቶቹን እንካችሁ ልላችሁ እችላለሁ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በግጥም የሚለግሰኝ ጥልቅ ምክሮች ዛሬ ላይ ብዙ ነገሮች እንዲቆጩኝ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ስለዛሬው የአብዛኞቻችን ሕይወት አስቸጋሪነትና በሁሉም ነገር ተወዳድሮ በላጭ መሆን እንደሚያስፈልግ በጥቂት ስንኝ እንዲህ እያለ ይተነብይልኝ ነበር እኔም አንዲት ሀረግ ሳልስት አስታውሳት ነበር፡፡
‹‹በእንዲህ ያለ ዘመን አይተኙም ይነቋል፤
በላተኛው ሁሉ በያፋፉ ዘልቋል››
ትላለች፡፡ ታድያ ይህች ግጥም ይህን ዘመን እንዴት ቁልጭ አርጋ እንደምታሳየን እናንተው ታዘቡ፡፡ሆኖም ግን ከብዙ ታላላቅ ትዝታዎቼ አንዱን ከአእምሮዬ ማህደር መዘዝ አድርጌ አዝናኝ የሆነውን የሕይወት ትምህርቴን ላጫውታችሁ፡፡
ወንድ አያቴና ሴት አያቴ ከትውልድ ስፍራቸው ተሰደው ኑሯቸውን ከሚመሩበት ትንሽ ወረዳ ወደ ኋላ በጊዜ ዥረት ልውሰዳችሁ፡፡ ተሰደውም መቂ ወረዳ በ ወዮ ገብርኤል መንደር ውስጥ መኖር የጀመሩት አያቶቼ ጋር የትምህርት ማለቅን ተከትሎ እረፍቴን ከእነርሱ ጋር ለማሳለፍና አየርና ቦታ ለመቀየር ብዙ ጊዜ ሔጃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይህ ክስተት ሲከሰት በጊዜው የ5ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርኩ ትዝ ይለኛል፡፡
አያቴ ወደ እርሻ ሲወጣ ሁልጊዜም ተከትዬው እሄድ ነበር፡፡ የገጠሩን ሕይወት ከማንም ባልተናነሰ የተማርኩበት ጊዜም እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ከአቦኖ ቀበሌ ጎን ካለችው የአያቶቼ መኖርያ በመነሳት በአካባቢው ሰንጥቆ የሚያልፈውን አስፓልት አቋርጠን በበቆሎ ማሳ ውስጥ እየተርመሰመስን እናልፍና በበቆሎው ወፍ መጠበቂያ ማማ ላይ ወጥተን ከእርቀት የሚታየንን የአዋሽ ወንዝ ቃኘት እያረግን ወፍ ስንጠብቅ ብዙ ወጎችን የምቃርምበት ሰዓታት ናቸው፡፡
ታድያ ከዕለታት በአንዲት ቀን ወደ ማሳው ስናመራ፤አያቴ ስለ አርጃኖ ባህርያት ብዙ እያብራራልኝ ነበር፡፡ እኔም በጉጉት ብዙ ጥያቄዎችን እያዥጎደጎድኩለት ወደ በቆሎው ማሳ ገባን፡፡ አያቴ ስለተፈጥሮ፣እንሰሳትና ስለ አካባቢው የነበረው እውቀት ከአንድ የጫካ መንገድ መሪ የአቦርዥን ወይም የቀይ ህንድ ጎሳ ጋር ልናመሳስለው እንችላለን፡፡ ወይ አባባ! ግርም ይለኛል ብዙ ነገሮቹን ሳስታውስ፡፡
እናላችሁ በዛች ቀን በማሳ ውሳጥ ስናልፍ አያቴ አንድ ነገር አስተዋለ፡፡ አንድ የማላውቀው እንሰሳ የእግር ዳና በመሬቱ ላይ ይታያል፡፡ አያቴ ሲነግረኝም፡፡ ‹‹ጉማሬ አለ፡፡ ኮቴው ትኩስ ነው፡፡›› አለኝ፡፡(ኮቴው ትኩስ ነው ማለት እንሰሳው በቅርብ ሰዓታት በቦታው እንዳለፈና በአካባቢው አሁንም ሊኖር እንደሚችል ለመግለጽ ነው፡፡)
በዚህ ጊዜ ትንሿ የልጅነት ልቤ ድንጋጤ ሰፈነባት፡፡ ምክንያቱም አያቴ አንዳንድ ስለጉማሬ የነገረኝ ባህሪያት ጥሩ ነገሮች እንዳልሆኑ ስለማስታውስ ነበር፡፡ አያቴ ምንም ሳይደናገጥ በእነዛ ጠንካራ እጆቹ ለስላሳውን የልጅነት እጄን ያዝ አድርጎ በቅርብ ወዳለ አንድ ማማ በፍጥነት ይዞኝ ወጣና በንቃት እርሻውን በአይኑ ይገረምም ጀመረ፡፡ድንገት ከወደ አንድ አቅጣጫ አንድ ነገር ሲርመሰመስ አየን፡፡ ልቤ መዝለል ጀመረች፡፡ ነገርዬው ብቅ ሲልም አንድ የአያቴ ወዳጅ የሆነ አርሶ አደር ነበር፡፡ አሁን ተረጋጋሁ፡፡
‹‹አያ አስፋው እንዴት ዋሉ››ካለ በኋላ መንገዱን ሊቀጥል ሲል አያቴ ‹‹ኸረ ተመለስ ጃል ጎማሬ ወጥቷል›› ሲለው፡፡
‹‹አይ እርስዎ ደግሞ ሁሌ ስለጥንቃቄ ነው ነገርዎ፤ምን ቢርበው ነው ጎማሬ ከባህር የሚወጣው›› ሲል ፈገግ እንዳለ አካፋውን ይዞ ወደ ገላጣው ሜዳ ማዝገም ሲጀምር አያቴም ለጠቅ አድርጎ፡፡
‹‹እኔ ነግሬያለሁ፤እውልኝ!›› አለው፡፡
በዚህ ወሬያቸው መካከል ከአርሶ አደሩ አቅጣጫ ፊት ለፊት አንድ ትልቅ ነገር ወጣ፡፡ አያቴ ‹የራበው ጎማሬ ከባህር ይወጣል፤ሰውም ይተናኮላል› ያለኝ ምክር ትዝ አለችኝ በዚህ ጊዜ፡፡ ጎማሬው ከአርሶ አደሩ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡ እንደ ጀግና ደረቱን ነፍቶ ሲሄድ የነበረው አርሶ አደር አሁን የድንጋጤ መንፈስ በልቡ ላይ የደም ያህል የረጨበት ይመስል ወዳላወቀው አቅጣጫ እግሬ አውጪኝ ማለት ሲጀምር ጉማሬውም ባለ በሌለ ጉልበቱ አርሶ አደሩን መከተል ጀመረ፡፡ አያቴና እኔ ማማው ላይ ሆነን መጯጯህ ጀመርን፡፡ ከምንም በላይ ግን ሳቄን መቆጣጠር የማልችልበት ትዕይንት ደግሞ እንደሚከተለው ተከሰተ፡፡
አርሶ አደሩ እግሮቹ ወዳልተረዱት አቅጣጫ ሲሮጥ፣ያጠለቀው ጫማ ከፊቱ ቀድሞት በአየር ላይ ሲበር፤ ጎማሬው ሲከተልውና አያቴም ድንገተኛ እርዳታውን ለመለገስ ‹‹ኩይሳው አፍር ስር ውደቅ›› ብሎ ሲጮህ እኔ በሳቅ እየፈረስኩ ነበር፡፡ በድንጋጤ ውስጥ ኩይሳው ስር የወደቀው አርሶ አደር በላዩ ላይ ጉማሬው ዘሎት ሲያልፍ አንድ ሆነ፡፡ እንደ አያቴ ምክር ከሆነም፡፡ ጉማሬ ከሰው እኩል መሮጥ የሚችል ጉልበተኛ እንሰሳ ነው፡፡ ጉማሬ ሲያሳድድህም በተቃራኒ አቅጠጫ መሮጥ ወይም መታጠፍ አልያም ጎድጓዳ ቦታ መተኛት ጉማሬን ለማምለጥ የሚረዱ ዘዴዎች ናቸው፡፡
ኩይሳው አፈር ስር ተደብቆ ጉማሬውን ያመለጠው ገበሬ፤ አያቴ ሲጠራው ከመደናገጡ የተነሳ ጫማውንና አካፋውን እንኳ ዞር ብሎ ሳያይ ወደ ቤቱ እንዳመራ ትዝ ይለኛል፡፡ እኔና አያቴም ማታ እሳት ዳር ቁጭ ብለን የምንጠብሰውን በቆሎ ሰብስበን እየተሳሳቅን ወደ አያቶቼ ጎጆ አመራን፡፡ ያኔ ማታ ትዕይንቱን በራሴ ፈጠራ በታከለበት የአወራር ስልት ለሴት አያቴ (አሁንም በሕይወት አለች) እሳት ዳር ቁጭ እንዳልን በልጅነት አንደበቴ እየተረኩ እንዳሳቅኳት አልረሳውም፤ አያቴም አይ ጋዜጠኛው! ሲል ያሾፈብኝን፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮም ጋዜጠኛው እያለ በቅፅል ስም ይጠራኝ ነበር፡፡ አያቴ እንደቀልድ የሰጠኝ ስያሜ ዛሬ ሞያዬ ሆነና አረፈው፡፡

Comments

Post a Comment

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?