ወይ ሃይስኩል


መቼም የሃይስኩል ትዝታዎች የሌለው ሀበሻ ማግኘት ባይከብድም፤ አብዛኞቻችን አልፈንበታል፡፡ ሃይስኩል ትዝ ሲለኝ ብዙ ነገሮች ከአንጎሌ የትዝታ ሳጥን ብቅ ይሉብኛል፡፡እኛ ካራማራ እንለዋለን አስተዳዳሪዎቹ ደግሞ ከፍተኛ 12 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ይሉታል፡፡ መቼም ፈረንሳይ ለጋሲዮንን ያየ ካራማራን ሳያይ አያልፍም፡፡ አሁንም ድረስ ማለት ይቻላል እነዛ የጡብ ሕንፃዎችን ሳይ ትዝ ትዝ የሚሉኝ ነገሮች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡
ካሯሯጡ የማይለቁ ሯጭ ዘበኞቻችንን ማን ይረሳል? እንደው እነ ደፈርሶ ያኑ ነቄ ቢሆኑ ኑሮ ተማሪ ከማሳደድ ጀምረው ዛሬ እንዴት የተዋጣላቸው አትሌት በሆኑ ነበር፡፡ ዱላ ካነሱ ሳይረበርቡን የማይመለሱ መምህራኖቻችንን ማን ይረሳል? ያቼን ሚኒሜዲያስ ብትሆን?...እንደውም ዛሬ ስለዛች ሚኒሚዲያ ሸረፍ አድርጌ አንድ ገጠመኝ እንካችሁ ልበል፡፡
ለነገሩ ለዛሬ ጋዜጠኝነት ለሚሉት ልክፍት የሆነ ሞያ የዳረችኝ ያቺ ሚኒ ሚዲያ ናት ብል አይጋነንም፡፡ ግን ብዙ ነገሮችን ተምሬባታለሁም ማለት እችላለሁ፡፡ ..እንደው አንዴ ምን ሆነ መሰላችሁ፤ እንደሚታወቀው የእረፍተ ሰዓት ላይ ሚኒሚዲያችን ትንግሳለች፡፡በወቅቱ የተጨበጨበላቸው የሚባሉ(የሚያጨበጭቡላቸው ጀሌ ተማሪዎች ስላሉ ነው) የት/ቤቱ ጋዜጠኞች ቀጥታ በሚተላለፍ ሙዚቃ ጀርባ ከባድ ጭቅጭቅ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እኔ ሆዬ አርፍጄ ወደ ስቱዲያችን(ይቅርታ ከ ስቱዲዩ ሌላ ቃል ስላጣሁ ነው) እየገባሁ ሳለ ወሬው ሳበኝና ሳቄን እንደያዝኩ ቆምኩ፤
ጭቅጭቁ ስለአንዲት የ9ኛ ክፍል ቆንጂት ነው፡፡ መቼስ የሴትና የወንድ ወሬ አይደለም በዛ እድሜ በዚህም ቢሆን ልብ ነው የሚያቆመው፡፡ እየተካረሩ እየተካረሩ ይመጣሉ፤ አስቂኙ ነገር ደግሞ ስለ ልጅቷ እና ስለአንደኛው የሚኒሜዲያው ጋዜጠኛ አደባባይ የማይወጣ ሚስጢር ነው፤ አጋጣሚ ሆኖ ልጅትም ይህንኑ ጭቅጭቅ ዝቅ ብሎ በሚንቆረቆረው የአስቴር ሙዚቃ ታጅቦ ትሰማ እንደነበረ በቅርብ ርቀት ይታየኛል፡፡ የግቢው ተማሪ ሁሉ ትኩረቱን ሚኒ ሚዲያው ላይ ያደረገ ይመስላል፡፡ ሁሉም ባለበት ሁኖ እየተሳሳቀና እየተሳቀቀ ይሰማል፡፡ ድንገት አንዲት ‹‹ክባድ›› የምንላት የ11ኛ ክፍል ተማሪ እየሮጠች በመግባት ጋዜጠኞቹን ገብታ ታቆማቸዋለች፡፡በዚህ ጊዜ ተማሪ ሁሉ ተበሳጨ፤ ክባድ ከስቱዲዮውም ስትወጣ የወንድ ተማሪዎች የተረብና የስድብ ሰለባ ሆነች፡፡
ሆኖም ወሬውም ሲቆም ዜማውም ሲቀየር፤ ተማሪው ሁሉ አጨበጨበ ከሳቅ ጋር፤ አንድ ተራቢ የሆነ የክላሳችን ልጅም ‹‹ቢስማርክ ይህ ፕሮግራም ሮብ ሮብ ነው የሚተላላፈው›› ሲል አሳቀኝ (ቢስማርክ ቅፅል ስሜ ነበር) እንደውም ስለ ቅፅል ስም አንድ የምላችሁ ይኖራል በቅርቡ ጠብቁኝ…እናላችሁ የዚያ ምስኪን ጋዜጠኛ ተማሪና የኮረዳዋ የፍቅር ታሪክ ግብዓተ መሬቱ የተፈፀመው ያኔ ነበር፡፡ በመቀጠልም እንዲህ ስል ስቱዲዮ ገብቼ አስተባበልኩኝ ‹‹አድማጮቻችን በተፈጠረው የቴክኒክ ችግር መተላለፍ የነበረበት ፕሮግራም ባለመተላለፉ በነገው ዕለት ጠብቁን›› አይ ጋዜጠኛ አያልቅበት ምክንያት!

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?