Posts

Showing posts from July, 2017

የሳውና ባዝ ትዝብቶች-ክፍል 4

እነሆ የሰው ልጅ በሁለት እንደሚከፈል ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት ሳውና ባዝ ስገባ ነው፡፡ ልብስ ሲለብስና ልብሱን ሲያወልቅ፡፡ ዛሬ እዚህ እየታዘብኩት ያለው ሰው ልብሱን ያወለቀውን የሰው ልጅ ነው፡፡ የሰው ልጅ ልብሱን፣ ዝናውን፣ዝናሩን ሲያወልቅ…ያው የሰው ልጅ ነው የሚመስለው፡፡ ያ ዓለምን የቀየረው፣ያ አራዊትን የገዛ፣ ያ ስልጣኔን የፈጠረ ፣ያ እራሱን ልዩ አድርጎ የሳለው የሰው ልጅ ልክ ልብሱን ሲያወልቅ ያው እንሰሳዊነቱ ይጎላል፡፡ ደሞ እኮ የሰውን ልጅ አካላዊ ቅርጽ ትክ ብዬ ሳየው ሌላኛው ግጣሙን ያላገኘ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ ይመስላል፡፡ ከራስ ጠጉሩ እስከ ራስ ጥፍሩ መግጠሚያውና መገጣጠሚያው ሌላ ቦታ የሆነ ሶኬት፣የሶኬት መቀበያ ወዘተ… አፉ ሶኬት፣ወንድነቱ ሶኬት፣ሴትነቱ ሶኬት፤ ብቻ የሰው ልጅ ወንድነቱን አውልቆ ሳ የው እሳታዊ ግጣሙ፤ኤሌክትሪካዊ አካሉ ከአንድ ቦታ ተነቅሎ ሌላኛውን ግጣሙን የሚፈልግ እቃ ይመስላል፡፡ ይቅርታ ይህን በራሴ ማየት ያልቻልኩት በኛ ሳውና ባዝ ክፍል ውስጥ መስታወት ባለመኖሩ ነው፡፡ ከፊት ለፊቴ መለመላውን የሚተራመሰው ሕዝበ አዳም ደግሞ ራሴን የማይበት በቂ መስታወት ነውና መስታወት ፍለጋ ምን ያደክመኛልስ? ዛሬ ከሳውና ባዝ ደምበኛና ወዳጄ ከድር ጋር ቁጭ ብዬ ነው ይህን የማውጠነጥነው፡፡ ሁለታችንም አቅም ስላነሰን ታችኛው ደረጃ ላይ ቁጭ ብለን ለብ ባለና ደረጃውን በጠበቀ ሙቀት እየተለበለብን ነው፡፡ ‹‹ዛሬ ደሞ ምንድን ነው ሁሉም ተፈራርቷል›› አለኝ ከድር፡፡ የሳውና ባዝ ጨዋታዎችን ልንቃርም እየጠበቅን፡፡ ‹‹ታገስ›› አልኩት ተዓምር የምጠብቅ እመስላለሁ፡፡ አጠገባችን የነበሩ ሁለት ጥርሰ ቡራቡሬ ሁለት ስክራፕ ሰጡን፡፡ ‹‹ይመቻቹ ያራዳ ልጆች›› አላቸው ከድር፤ አንደኛው የቡና ማልያ የመሰለ ጥርሱን ብልጭ አርጎ ‹‹ኸረ እኛ የመታ