ያኔ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ሰሞን


መቼም እንደያኔው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የጦቢያ ባንዲራና የዋልያዎቹ መለዮ በቲሸርት፣በቁምጣ፣በቦዲ.. በፕላስቲክ አንባር ጠንከር ሲልም ግልጥ በሚታዩ ልባሶች፣ ጡት ማስያዥያ የሚመስሉ ነገሮች ሳይቀሩ ማለት ነው፡፡
ያኔ የተለመደውን ዙሪቴን ለማድረግ በአራት ኪሎ በኩል ወዳጆቼን ለማግኘት ዘልቄ ነበር፡፡ ነገር ግን የወዳጄቼን መቆየት አስታክኬ አንድ ጥግ ላይ ቁጭ ብለው ‹‹እ!..አለ የሚቀባ..ቀለም፣ቀለም…›› የሚሉ ወጣቶች ልጆች ወሬያቸው ሳበኝና ጠጋ ከማለቴ፣
‹‹ነይ ቀዮ ይህን ቀይ ፌስሽን ላሸብርቀው በናት ሀገራችን ቀለም!››
ሳቅ እንደያዘኝ ‹‹ አታሸብርቀው ..ግን ሰው እየጠበቅኩነው፤ሰትቀቡም ለማየት ነው›› አልኩት
‹‹አብሽር ዱቅ በይ›› አለኝ፡፡ ቀለሙ ከምን እንደሚሠራ፣ማን እንዳመጣው ባይገባቸውም ብቻ ለዛሬም ቢሆን ለነዚህ ወጣቶች ትልቅ ገቢ ነው፡፡
ከሌላ አቅጣጫ ፊቱን በቀለም አዥጎርጉሮ የሚመጣውን ጓደኛቸውን ሲያዩት ፣ተንጫጩ፣የተረብ ናዳውን አወረዱት፤
‹‹አንተ አንገትህን ዝቅ አግርገው ነው እንዴ የነከሩህ›› አለው አንዱ
ሌላኛው ‹‹ ኒያላ ነው የምትመስለው እንኳን ዋልያ ልትመስል››
 አንዱ ተቀበለና ‹‹አንተ እኮ ባትቀባም ዋልያ ትመስላለህ›› ፤ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ…
                                          ‹ለከፋና  ሽቀላ››
 እንዴት እንደሆነ ባይገባኝም ለከፋና ሽቀላ አብረው የሚሄዱ የዘመኑ ትዕይንቶች ናቸው፡፡ ቀለም ከሚቀቡት ወጣቶች አንደኛው አፉ የማያርፍ ዓይነት ነው፡፡ አላፊ አግዳመውን ለቀለም ከመጋበዝ ባለፈ ተረብም ጣል ያደርጋል፡፡ አንዲት ኮረዳ ቢጤ ብቅ ስትል፤
‹‹እናቱ ልቀባልሽ…ውይ ይቅርታ ልቀባሽ›› ተሳሳቁ፡፡ በግልምጫ አንስታው አለፈች፡፡
ሌላኛዋ መጣች ‹‹ጭሷ አትቀቢም?››
‹‹አመሰግናለሁ›› እየተመናቀረች ስታልፍ ‹፣ተይ ለናት ሀገርሽ ነው!..ተይ ግን ?››
‹‹እንኳን! ወርቅ የምትቀባኝ መሰለህ?›› ስትለው
ውይ ውይ ሴቶች ለምንድን ነው ነገሮችን ሁሉ ከገንዘብ ጋር የማታያይዙት›› አለ ጮቅ ብሎ፡፡ ሁላችንንም ፈገግ ለማድረግ ያለመ ይመስላል፡፡ ልጅትም በዝማታ እንዳልሰማች አለፈች፡፡
እንዲህ አላፊ አግዳሚውን እየጠየቀ ድንገት አንዲት የሃበሻ ማልያ ያደረገች ወጣት መጣች፣ፊቷ በቀለም ተዥጎርጉሯል፡፡ ይህችን ሴት ብቻ በነገር በእንካ ሰላንትያው ግጥሚያ ሊቋቋማት አልቻለም በመጨረሻ ላይም
‹‹ቆይ አንቺ ሴቷ ዋልያ!...ትመለሻለሽ እኮ!..አገኝሻለሁ›› ከማለቱ
‹‹ ተው ባክህ ወንዱ ዋልያ…ምን ልታረገኝ? በቀንድህ ልትወጋኝ?›› ይሄን ጊዜ እኔም ሳቄ አመለጠኝ
‹‹ ኸረ በቃኝ!...ኸረ በቃኝ አንቺን መቼም አልችልሽም…ክንድ ምላስሽን ዘረጋሽው እኮ ›› አለ እጁን ወደላይ እያወራጨ፡፡
ስልኬ አቃጨለች፡፡ መሄዴ ግድ ሆነና ተሰናብቻቸው ሄድኩ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?