የሳውና ባዝ ትዝብቶች


የፍልውሃ ደንበኛ ነኝ፡፡ ቋሚ ተሰላፊ ነኝ ማለትም እችላለሁ፡፡ ምንስ ቢሆን የነጣይቱን ያህል በተፈጥሮ ፍል ውሃ ባንገለገልም በኤሌክትሪክ ፍሊትም እንቀቀል እንጂ፡፡ አሁን አሁን ግን ቤቱ እርጅና ተጭኖት ብዙው መገልገያቹ አርጅተው፤ ፍልውሃ ከተገለገሉ በኋላ ቤትዎ ሄደው ሸውራራ ሻወር እንዲወስዱ የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ያም ሆነ ይህ ከሳውና ባዝ በየጊዜው የቃረምኳቸው ትዝብቶች ብዙ ናቸው፡፡ በመሰረቱ ሳውና ባዝ ሆነም ሌሎች የእጥበት ሥርዓቶች ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ገና በ11ኛው ክፍለ ዘመን በጎንደራውያን የስልጣኔ እርከን መሆኑን ምን ያህሎቻችሁ እንደምታውቁ ባላውቅም የጎንደርን ቤተመንግስት የጎበኘ ግን ይህንን ነገር ማወቅ ይችላል፡፡ እነ ፋርስ፣ህንድ፣ቻይና እና የአረብ ምድር እኩል ከኛ ጋር ይህን የስልጣኔ ትሩፋት ኮምኩሟል፡፡
ታሪክ ማውሳቱን እንተወውና ወደ አዲስ አበቤዎች የሳውና ባዝ ተጠቃሚዎች ልምጣ፡፡ በዛች ጠባብ ክፍል ውስጥ በወንዶች ክፍል የሚታየውን ትዕይንት እኔ ላካፍላችሁ፤በሴቶቹ በኩል ያለውን እንስት ፀሐፍት ተገኝታ እስክታካፍላችሁ ጠብቁ፡፡ እናላችሁ ገና ከመታጠቢያ ገንዳው ሳይደርሱ የሚታዘቡት አዝናኝ ምስል ፈገግታን በነጻ ይስኮመኩምዎታል፤ጥርብ እግር፣ፍልጥ እግር፣ግንድ እግር አልያም ደግሞ የወንድ ነፍሰ ጡር የሚመስል በደምሳሰው ደግሞ ፤3 ቁጥር 9 ቁጥር፣ 10 ቁጥር እንደው ምን አለፋችሁ የተለያዩ የአረብኛውን ቁጥር የሚወክሉ ቅርፅ ያላቸው ወጣቶች፣አዛውንትና ጎልማሶችን እያያችሁ፤ሀበሻና ስፖርት ጠብ ውስጥ እንደሆኑ ስትረዱ ፈገግ ይላሉ፡፡
ወደ መታጠቢያው ገንዳ ሲያመሩ ደግሞ የሚያዩት ትዕይንት ፈገግታ ብቻ ላይፈጥርብዎ ይችላልና እንደመሳቅ ሊቃጣዎም ይችላል፡፡ የሰዎቻችን የአስተጣጠብ ክህሎት ሀበሾች የውሃ ዕጥረት በጣም እንደሚያጠቃቸው ልብ ይላሉ፡፡ ለነገሩ የሚፈሱ ወንዞች እንጂ የምነጠቀምበት የለን፡፡እርግጥ ነው የአስተጣጠብ ህግና ደንብ የለውም ነገር ግን አብዛኞቻችን ስንታጠብ ታውቆንም ሳይታወቀን ይሁን በገላችን ላይ የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ የጭቆናና የአፈና ስራ እንደፈፅምበታለን፤ለነገሩ ከማን እንማረው እንዳስተማሩንስ አይደል፣እኛን እንደሚያደርጉን አይደል የምንኖረው…
እናላችሁ ከሚያስቁኝ አስተጣጠቦች መካከል ልጠቃቅስላችሁ፡፡ አብዛኛው ተገልጋይ ላይ የማየው የአስተጣጠብ ክህሎት መታጠብ ሳይሆን ከራስ ቆዳ ጋር ግብግብ መፍጠር ይመስላል፤የሚታሸውም ቆዳ የታፈነ ጩኸት ሲያሰማ እንታዘባለን፤ አንዳንዱ ደግሞ ከሰውነቱ ሁሉ ጀርባው ላይ የሆነ መንፈስ የተከመረ ይመስል በቡጭሪያ አይሉት በቁንጥጫ ልምዝግ አድርጎ ቆዳውን አዞ የሄደበት መንገድ ያስመስለዋል፤ሌላው አይነት አስተጣጠብ ደግሞ በዘፈነ የታጀበ ነው፡፡ ውሃ ሲነካው ዘራፍ ማለት የሚቀድመው አይነት ሰው መሆን አለበት፤ እንጉርጉሮውን ሲያወርደው ድምጡ ጆሮዎን ወዲያው እንዲታጠቡት የሚያስገድድ አደጋ ሊፈጥርብዎት ይችላል፡፡ ውሃ ፈውስ ነው፡፡ ውሃ የሰውነት ጉድፍ ብቻ ሳይሆን የአንጎል ድክመትን የሚያረግብ ምስጢራዊ የሆነ የዚች ብቸኛ አለም ስጦታ ነው፡፡ እያንዳንዷን የውሃ ጠብታን በተመሥጦ ልንዋሃዳት ይገባል፡፡ መፅዳት ማለት እኮ እንዲህም ነው፡፡
አለላችሁ ደግሞ ሸንጎበቱን የሚያራግፍ የሚመስል፤ይህ አይነቱማ ከመታጠብ ይልቅ እየተርገፈገፈ የሚጨርሰው ጉልበቱንና ውሃውን ብቻ ነው የሚያሳዝነኝ፡፡ እጅግ ለወሬ የፈጠነው ደግሞ ገላውን ሳሙና መትቶ አንድ ዓይኑን ግድል አድርጎ በሌላኛው አይን እያየ፤ ውሃን እንደከፈተ እኩል አፉን ይከፍታል፤ውሃውም በከንቱ ይፈሳል፤ ለነገሩ ዕድሜም በከንቱ የሚፈስበት ሀገር ነውና የውሃው መፍሰስ ላይደንቀን ይችላል፡፡ አንዴ ያየሁት አስጠተጣጠብ ደግሞ ገራሚ ነው፡፡ ሰውዬው ጭቅቅቱን የሚያራግፍ ሳይሆን ከገላው ጋር ጭቅጭቅ የያዘ ይመስላል፡፡ አሁንም በፈገግታ መቃኘቴን አላቆምኩም፡፡
ፎጣ መጠቀም የማይወድም አሉላችሁ፡፡ ይህ ዓይነቱ ደግሞ በሳውና እሳት ተዳክሞ ማረፊያው ክፍል ከተሰበሰበው ወፈ ሰማይ ሕዝብ መሃል በትረ መኮንኑን እንዳንጠለጠለ መለመላው ሲንጎራደድላችሁ የሳውና ባዝ ዥግና ሊሉት ይቃጣዎታል፡፡ ይህ ትዕይንት ግን ከሌሎቹ በበለጠ እጅግ የሚያስቀኝ ነው፡፡
ወደ መቃጠያው ክፍል ይዣችሁ ደግሞ ልግባ፡፡ ይህ ክፍል በአሮጌ ጣውላዎች የታጠረ የዶሮ ቆጥ ይመስላል፡፡ ሁሉም ተጠቃሚ ቆጡ ላይ ፊጢጥ ብሎ ይወጣና በእሳት ይለበለባል፡፡የበሰለው ቀድሞ ይወጣል፤አኞ የሆነው እዛው ይቆያል ማለት ነው፡፡ የኛን ሳውና ባዝ ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ወግ፣ጨዋታና ክርክሩ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚካሄዱት ክርክሮች በቤተሰብ፣ትዳር፣ሴትና ወንድ፣ወሲብ፣ሐይማኖት፣ፖለቲካ፣ስፖርት (የአውሮፓ ኳስ) ናቸው፡፡
የሆነው ሆኖ ክርክሩ ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን የኛ ሰው ክርክር ላይ ያለው አቋም ከሌላው የዓለም ሕዝብ የተለየ ይመስለኛል፡፡ ግድ አንደኛው መሸነፍ አለበት በሚል ሰጣ ገባ ውስጥ ፀብም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ክርክር መማማሪያ ነው የሚለው ነገር አስቀድሞ ይወገዳል፡፡ መደማመጥ የለም፤የጨበራ ተዝካር ይመስላል፡፡ አንዳንዶች የሌላኛውን ወገን ሃሳብ መቀበል ካልፈለጉና የነሱን ሃሳብ የሚያስንቅ ከመሰላቸው አንድ ላይ ይጮሃሉ፣ያውካካሉ ተናጋሪውም ሃሳቡ ሳይሰማለት ተናዶ ሊወጣም ይችላል፡፡‹‹ignorants are certain and happy›› የሚለው የፕሮፌሰሩ አባባል እዚህ ላይ ትዝ ይለኛል፡፡
አንዴ የገጠመኝን ላውጋችሁ፡፡ በአንድ የሕክምና ጋዜጣ(ሜዲካል) የወጣ ፁሑፍ ላይ ሁለት ጠብደል ያሉ ወጣቶች እየተከራከሩ ነው፡፡ በወቅቱ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ እንደነበርኩ ትዝ ይለኛል፡፡ የሚከራከሩበትንም ፁሑፍ አውቀው ነበር፡፡ እኔን እዛው ቁጭ አርገው ፀሐፊውን ይቦጭቁታል፡፡ ለነገሩ ሳይንስ የኛ ሰው መሃል የማይወራ ጉዳይ ነው፡፡ በኋላ ላይ እነዚህ ልጆች ተካረሩና ከመቃጠያው ሲወጡ ግብግብ ገጠሙ፡፡ እናንተዬ ላካ ሰው ራቁቱን ሲደባደብ እንዲህ ያስቃል?...ደግሞ እኮ ሁለቱም ስለሚሙለጨለጩ ለማገላገልም አይመቹም፡፡ ቂቂቂ… እነሱም ቢሆኑ በጣም አልተጎዳዱም፤ ሳሙናና ላቡን ማን ይያዘውና? ቂቂቂ…
በአጠቃላይ ግን ይህ ሕዝብ ሳውና ባዝን ከዓለም ቀድሞ የጀመረ አይመስል፡፡ የ11ኛው ክ/ዘመን ጎንደራውያን ነገስታትና ነዋሪዎች የአዲስ አበቤን ሳውና ባዝ ተገልጋይ ቢያዩ እንዴት በሳቁ ነበር፡፡ እኔ ግን ትዕይንቱን እየታዘብኩ ይኸው እስከዛሬ አለሁ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?