ልጅነታቸውን የተቀሙ ልጆች
ሁሌም ወደ ቢሮዬ ሳመራ ብሔራዊ አካባቢ የማየው አንድ ትዕይንት አለ፡፡ አሁን አሁን የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በታክሲ ውስጥ ሳልፍ፤‹ምነው እነዚህን መንግስት ዝም አላቸው› የሚለው ተሳፋሪ ብዙ ነው፤ አንዳንዱ ደግሞ ‹እነዚህንማ አንድ ቦታ ወስዶ ማጎር ነው!›ይላል እናንተም ሳታዩዋቸው አትቀሩም…
ቁጥራቸው ከዕለት ዕለት እየጨመረ መጥቷል፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ራሳቸውን እንደሚጠሩት ‹ቦርኮዎች› እዚህ ብሔራዊ አካባቢ ባሉ የትራፊክ መብራቶች ሥር ቁጭ ብለው መብራት የያዘውን መኪና ጠጋ በማለት የፊት መስኮቶቹን በመወልወል ሳንቲም ይለምናሉ፤ ታዲያ ይህ ምኑ ይገርማል እንዳትሉኝ፤ ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡
እነዚህ ሕፃናት ከትንሽ ትልቁ ሁሉም እጅ ላይ አንድ ነገር አይጠፋም፤በተጎረደ ሃይላንድ የተሞላ ማስቲሽ፡፡ ባለፈው እንደተለመደው ወደ ቢሮ ሳመራ መብራት ያዘን፤ድንገት ከየት መጡ ሳንለው ወረሩን፤ሊያባርረቸው የሚወራጨውን ሹፊራችንን ‹‹ተዋቸው›› አልኩና የመኪናውን መስታወት ወልውሎ እጁን ለሳንቲም የዘረጋውን ታዳጊ መስታወቱን ዝቅ አድርጌ ጠራሁት፤ ሰፍ ብሎ ሲመጣ አንድ ብር ስሰጠው፤
‹‹ይመችሽ ያራዳ ልጅ የገባሽ ነሽ እኮ›› ምርቃት እንደሆነ የገባኝ ከዚህ ሌላ ምንም የሚለኝ እንደሌለ ስገነዘብ ነው
‹‹እሱ የያዝከው ነገር ምንድን ነው?››
‹‹አታርፊውም እንዴ ጀለስ፣ማስቲሽ ነው እኮ›› አለኝ
‹‹ምን ያረግላችኋል?››
‹‹ኸረ ሙድ እየያዝሽ መሆን አለበት ፤ያራዳ ልጅ አይደለሽ እንዴት አታርፊም፤ምግብ እኮ ነው!›› ያራዳ ልጅ ልሁን አልሁን አሁን ይህን ከዚህ ጋር ምን ያገናኘዋል አልኩና ለራሴ፤ማስቲሽ ያለው ኬሚካላዊ ይዘት ርሃብን ከማስቀረት አንፃር እሚያስረዳኝ ሰው ባለመኖሩ ግራ እንደተጋባሁ ሳስብ፤
‹‹ማስቲሽ ካልሳብንማ አለቀልን ማለት ነው›› የፌዝ ፈገግታ ፈገግ ሲል ድንገት ጥርሱ ላይ የሆነ ነገር ያያሁ ስለመሰለኝ
‹‹የአዲስ አበባ ልጅ አይደለህም አይደል?››
‹‹ኸረ ምን በወጣኝ..›› ሁሉም ሳቁ ሌላኛው ተቀበለና ‹‹የመተሃራ ልጅ ነው›› ሲል ‹‹ ሂድ አንተስ ከየት መጣህና›› መሰዳደብ ጀመሩ ፣ጣልቃ ገባሁና ፣
ሌሎቹስ ብዬ ከመጠየቄ ‹‹ናዝሬት፣ዝዋይ..ምናምን…››
ለመሆኑ የማስቲሽን ጥቅም ማን በዚህ መልኩ አሰበው፣ማንኛቸውስ ጀመሩት፣እንዴትና ከየት ያመጡታል፣ ይገዙታል የሚሉ ጥያቄዎች ቢመጡብኝም ያለኝ ሰዓት ትንሽ ነበርና
‹‹እዚህ እንዴት መጣችሁ ›› ስል ቀጠልኩ
‹‹ጢሎ ብለን›› አንዱ ሲጀምር ሌላኛው...‹‹በመኪና አርፋ ብለሽ አታውቂም ነብሱ..›› በጥያቄ መልኩ አብራራልኝ፡፡ ድሮ ልጅ እያለን በመኪና አርፋ ብንልም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎሜትሮች እንዳልሄድን ግን እርግጠኛ ነበርኩና ፈገግ አልኩ፤
መብራቱ አረንጓዴ ሳይል አንድ ጥያቄ መጣልኝና
‹‹ እነዛ ልጆችስ›› በእጄ እየጠቆምኩ
‹‹ችኮቹ›› ጠየቁኝ ፤በመስማማት አንገቴን ነቀነቅኩ ‹‹ሁሉም ይስባል የማይስብ የለም›› አንዱ መለሰ
ሌላኛው ‹‹ኸረ ፈጋሚዎች ናቸው፤ ከነሱ ጋር መሳፈጥ የለም››(አጫሾች ናቸው ማለቱ ነው) ሲል
‹‹የቅድሙ ልጅ ተቀብለውና ‹‹ ሂድ አንተስ አትፈግምም! ሲል አፈጠጠበት ድጋሚ መሰዳደብ ጀመሩ፤ እናትህን እንዲህ ላርጋት፣እናትህ እንዲህ ትሁን፤ፀብ መሰል ልፊያ ጀመሩ፤
አረንጓዴ መብራት በራ፡፡ እኛም በ ኢቲቪ በራፍ አለፍን፡፡ ይህን የመሰለ የፈጠጠ ችግር ኢቲቪ አፍንጫ ስር መኖሩ ፈገግ ያሰኛል፡፡ እናንተዬ ኢቲቪ በራፍ ላይ ያላስተዋልኩት ነገር ድንገት ያየሁ ሁሉ መሰለኝ ‹‹ኢቲቪ እንዲህ እንደ ኢምባሲ መቼ ነው መጠበቅ የጀመረው? ›› አልኩ ለራሴ፤ የታጠቁ ወታደሮች፣ሰሪቪሊያንስ ካሜራ፣የአጥር ስፖክዮ…አይ እንግዲህ ወደ ቦለቲካው ሳልዞር ታዳጊቹም የተቀሙን ልጅነታቸውን ፈልገው ያገኙት ዘንድ እየተመኘሁ እዚህ ላይ ቢበቃኝስ…
Comments
Post a Comment