አቦን ያየ በልጥ በረየ
ጊዜው ከሰማንያዎቹ መጨረሻ አለፍ ብሎ ከዘጠናዎቹ መጀመርያ ውስጥ ነው፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ካሏት ት/ቤቶች ሁሉ ለየት ያለ ነው፤አቦ ት/ቤት፡፡ እኛ አቦ ት/ቤት ስንለው መስራቹ ደርግ ደግሞ መካነ ሕይወት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ብሎ ሰይሞት እንደነበረ በሩ ላይ የተደነገረው ጹኹፍ ይመሰክራል፡፡
አቦ ት/ቤት ከአቡዬ ቤተ ክርስቲያን ጎን በመሠራቱና ቀደም ሲል ቦታው የቤተክርስቲያኑ መቃብር የነበረ ሲሆን ደርግ መቃብሩን በማረስ ት/ቤቱን እንደገነባበት ይነገራል፡፡ ታድያ በዚህ ት/ቤት እንደማንኛውም የፈረንሳይ ልጅ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ትምህርቴን ተከታትያለሁ፡፡ አቦ (ት/ቤቱን ነው) በባህሪው ወልዶ መጣያ እንደሚባሉት ዓይነት ነበር፤የዛሬን አያርገውና! የትኛውም ወላጅ ልጁን እየሱስ 41 ወደሚገኘው ሚሽን ት/ቤት ለማስተማር ይሞክራል፡፡ በዘመድ አፈላልጎም ቢሆን፤ካልሆነ ወደ አቦ ጦር ሜዳ ስንቁን አስይዞ መላክ ነው፡፡አጥር የሌለው፣ መስኮቶቹ የተሰባበሩ፣ነውጠኛ ተማሪዎች የሚማሩበት፤በተለይ የአቦ ሰፈር ዱርዬዎችን ያፈራ እንደሆነ የት/ቤቱ ታሪክ ይጠቁመናል፡፡
ታድያ ይህን ካልኳችሁ በአንድ ወቅት የገጠመኝን፣አስቂኝ፣አስደንጋጭና በት/ቤቱ ወሳኝ ለውጥን ያመጣ ክስተት ላውጋችሁ፡፡
7ኛ ክፍል እያለን እጅጉን ደስታ ከሚሰጡን ነገሮች መካከል ኳስ መጫወትና ኳስ መጫወት ነው፡፡ ታድያ የኛ 7ኤ ክፍል ደግሞ እጅጉን የለየለት ረባሽ፣ ደስታና ጨዋታን የሚመርጡ ታዳጊዎች የተሰባሰብንበት ክፍል ነበር፡፡ ጥሎብኝ ሁልጊዜም ረባሽ ክፍል ይደርሰኛል፡፡ ማን ያውቃል ረብሻው ጥሎበት ሁሌ እኔ አጋጥመው ይሆናል፡፡ ባገኘነው አጋጣሚም በት/ቤቱ የታችኛው ክፍል ወርደን እንጫወታለን፤እንራገጣለን፤ላባችን ጠብ እስኪል እንፈነጥዛለን፤ነገ መኖር እሚሉት ሀሳብ እንደሌለ እስክንዘነጋ ድረስ የደስታን ጫፍ ለመንካት እንባዝናለን፡፡
ታድያ ከትምህርት ቀናት በአንዷ ዕለት መምህር ባለመኖሩ ቅሪላ ለመግፋት እኛ 7ኤዎች ተሰባስበናል፡፡ ጨዋታው ደርቷል፡፡ ላይ ታች የማይል ማንም አልነበረም፡፡ ከኛ በቅርብ ርቀት ደግሞ የክፍላችን እንስቶች ግማሾቹ ሱዚ ግማሾቹ ገመድ፣ቃጤ እየተጫወቱ ነበር፡፡ ለነገሩ የሴቶቹ ጨዋታ የሚመስጣቸውም ወንዶችም አሉላቹ እኩል ከሴቶቹ ጋር ሲ! እያሉ የሚጮሁ፡፡ እንደው እናንተዬ የዘንድሮ ዘመን ታዳጊ እንስቶችን ሳስብ ከጊዜው ቀድመው የተለወጡ ይመስለኛል፡፡ እነዚህን መሰል ጨዋታዎች ገና በኬጂ ደረጃ እርግፍ አድርገው ትተው ጨዋታቸው ሌላ ነው የዘንድሮዎቹማ፡፡
ጨዋታው ደርቷል፡፡ ድንገት የሆነ ሰዓት ላይ ፎሪ የወጣ ኳስ ለማምጣት ሁለት ተቃራኒ ቡድን የሆኑ ልጆች፤ሳሚ እና በቅጠል ስሙ አይናማው የምንለው ተማሪ ኳሳን ለመያዝ ፎሪ የወጣበት ቦታ ላይ ይሻኮታሉ፤ እኛ ደግሞ ኳሷ ፎሪ ናት እያልን እንጮሃለን፡፡
ድንገት አይናማው አንድ እግሩ እጥር፣እጥር እያለ ሲመጣ ይታየናል፤ ግራ ተጋብተን ሁላችንም እናያለን፣ መሬቱ ላይ ሁለቱም እንደተያያዙ ዘጭ ሲሉ ይታየናል፤ ምን እንደሚያዩና እንደሚያወሩ ባይገባንም የአይናማውን እግር እግሩን እያዩ እንደሆነ ይታየናል፡፡ ሳሚ ጩኸቱን አቀለጠው፣ ወደኛ እየተርበትበት እየሮጠ መጣ፣ አይናማው በዳዴ እንደምንም ከወደቀበት ቦታ ለመራቅ እየተውተረተረ በጩኸት ወደኛ ለመምጣት ይሞክራል፡፡
‹‹ምንድን ነው?›› ሁላችንም ጥያቄውን አዥጎደጎድነው
‹‹እሩጡ፣ እሩጡ፤ አምልጡ!›› ሳሚ ወደኛ እየሮጠ መጣ፡፡ ወይ የጉድ ሃገር!፤አይ የልጅ ነገር ማጣራት የለ፤ሁላችንም እየጮህን መሮጥ ጀመርን፤ የኛን መሮጥ ያዩት ሴቶቻችን ፤ ከፊታችን ቀድመው መሮጥ ጀመሩ፤ እንዲህ አይነት የድንጋጤ እሩጫ በት/ቤቱ ታሪክ ቢመዘገብ አንደኛ እንደሚሆንና በዓይነቱም ለየት ያለ እንደነበረ ታሪክ ይዘክረው ነበር፡፡
ቢሮ አካባቢ ስንደርስ፤ዞር ብለን ስናይ የሚከተልን ምንም ነገር ባለመኖሩ
‹‹ምንአባህ ሆነህ ነው? ምንድን ነው?›› ሳሚን ሁላችንም አፋጠጥነው
ትንፋሹን ለመሰብሰብ እየሞከረና እየተርበተበተ ‹‹ሰውዬው..ሰ..ሰውዬው እዛ ጋር አለ››
‹‹የምን ሰውዬ?››
‹‹አይናማው እግሩ የሰመጠበት ቦታ ውስጥ ሰውዬው ተኝቷል፤ ማ..ማለት ሬሳው አለ..ማለት አፅሙ አለ››
‹‹ምን?›› ‹‹ምን?›› ሁላችንም ጠየቅነው፡፡ ‹‹እና ለዛ ነው እንደዚህ ያስሮጥከን›› ሰደብነው፤ወረድንበት፤ሴቶቹ ሁሉ ሳይቀሩ ሳሚ ፈሪው ሲሉ ተሳለቁበት፡፡
ከዛ በኋላ እንደምንም እግሩን ጎትቶ እየተርበተበተ የመጣው አይናማው ግን አሁንም አልተረጋጋም፡፡ እኛ ስንስቅበት ለመረጋጋት ሞከረ እንጂ ከልቡ ተንጰርጵሮ ነበር፡፡ በተለይ ግራ እግሩ ይንቀጠቀጥ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡
ትንሽ ደፈር የምንል ልጆች ተሰባስበን ሄደን ለማየት ጓጓን፡፡ ሄድን፡፡
ሁላችንም አፅሙን ከበን ማየት ጀመርን፡፡…‹‹አንተ ተው እንዳትነካው!›› የክፍል አለቃችን ተቆጣ
‹‹ዋ!›› ሌላኛው አስፈራራ
‹‹መንፈስ ቢኖረውስ›› ፍልስፍና የማያጣው አንድ ተማሪ ነበር እንዲህ ያለው ደግሞ
ያኔ የ7ኛ ኤ ተማሪዎች የሰው አፅም ለመጀመርያ ጊዜ ስናይ እንደሆነ ጥርጥር አልነበረውም፡፡ ሳሚና አይናማው ኳሷን ለመያዝ የሬሳው ሳጥን ላይ እጅግ በመሻኮታቸውና የአይናማው እግር በሳጥኑ ቀዳዳ ቀዶ ሲገባ፣ እግሩን ለማውጣት ሲታገል ሳጥኑ ባብዛኛው መከፈቱና የተወሰነ የእግርና እጅ አጥንት ሳሚም አይናማውም በስህተትና ሳያስቡት መንካታቸው ነበር፡፡ ለዛ ሩጫ የዳረገን፡፡
ጉዳዩን የሰማው ዳይሬክተራችን ፖሊስ በማስመጣት አፅሙ እንዲነሳ አደረገ፡፡ ከጊዜ በኋላም አጥሩ እንዲታጠርና መሬቱ እንዲደለደል አደረገ ፤ይህም ሌሎች አፅሞች ሊኖሩ ስለሚችሉም በማሰብ ነበር፡፡ ይህ እስኪፈጸም ድረስ ግን ለተወሰነ ጊዜ ታችኛው ሜዳ ላይ ኳስ መጫወት ቀርቶም ነበር፡፡ እባብን ያየ በልጥ በረየ እንዲሉ አቦ ት/ቤትን ያየ ደግሞ በሰው አፅምና ሬሳ ድንጉጥነቱን ይፈትናል ይሏል 7ኛ ኤዎች ሲተርቱ፡፡
Comments
Post a Comment