Posts

Showing posts from 2016

የቀዮች ጉዳይ

ዘወትር በሀበሻ ዜማ ውስጥ የምሰማው ለሀበሻ መልኮች፤ ውበት የተዘሜመ ስንኝ…በአማርኛ ብቻም ሳይሆን በሌሎቹ ቋንቋዎች…ጠይም..ጠይም አሳ መሳይ… ጠይም ናት ጠይም መልከ ሸጋ… ጥቁር ሰው… እንደጸሐይ የሚያበራው ጥቁር ውበቱ…ጠየም ያለ ሎጋ… ፒሪሪም ፒሪሪም.. ወዘተ…እኔ የምለው ግን ለቀይ ሰውስ? ቀይ ዳማ እንኳን ባቅሟ ተዚሞላታል…ለቀይ ሰው የተዜማ ነገር መፈለግ ዘበት ነው…ቢኖርም እንደው ለሞራላቸው/ችን እንጂ...ብቻ ቀይ ሰዎች የአገሪቱ ጠላት ዜጎች፤ወይም መጤዎች ይመስላሉ!   ግን አንድ ሁለት ትዝ የሚሉኝ ስንኞች… አንዱ ያላለቀ ስንኝ ነው ‹‹ቀይ የወደደና እባብ የነደፈው….›› ቤት መምቻው ተረስቶኛል…ያስታወሰው ይምታበት… ሌላ አንድ የሙሉ ቀን ዜማ አለች ደሞ…. ከወደዱም አይቀር ይወዳሉ ቀይ                                     እንዳላማ ሰንደቅ ከሩቅ የሚታይ ቤት መምቻው በግድ የተወረወረ ይመስላል፤ እንዲገጥምለት ብሎ ነው ልብል? ግጥሙ እንዲመታለት ብሎ እንጂ ቀይ ሰውን ለማድነቅ አይመስልም… እንደውም በዚህ ስንኝ ዝርው ውስጥ ከቀይ ሰው ይልቅ የሰንደቅ አላማው ድምቀት የጎላ ነው… ያሳዝናል፤አንድ እኛን የሚወክል ምርጥ ስንኝ ይጥፋ? አለ አንድ ቀይ ወዳጄ፤በቅጽል ስሞ ሶላቶ... ደሞ ጉድ እኮ ነው…ትንሽ ቀላ ያለ ሰው ስድቡ መከራ ነው…እኛ ጥልያንን ስለምናስታውሳቹ እንዲህ ጠመዳችሁን! አለ ይሄው ሶላቶው ወዳጄ…ቅናት ነው ልብል?! እስኪ ስንኝ አዋጡ ለቀያዮቹ አበሾች…? መፈክር እንዳታደርጉት ግን አደራ በቀዮ ይዣችኋለሁ!በዚህም ቀንታችሁ ነው እንዳትባሉ…

ርዕስ አልባ ግጥሞች

ዝምምም…ባለ ዝምታ ስጥምምም..ባለ ፀጥታ አንድ ገጽ አለ… የልብ ድቢ የሚያስመታ ከእርጋታው ፊት ለፊት ትክዝዝ… ካለው ሽፋሽፍት አንድ ገጽ አለ… ልብ የሚያሸፍት ከፀዓዳው ጉንጭ፤ከጸዓዳው ከንፈር ስር አንድ ማህሌታይ አለ የሚንዠረዠር ሳይጻፍ ሳይነገር… ዝምታም እንዲህ ይፈሳል.. ማቀርቀርም እንዲህ ይወርዳል… ትካዜም እንዲህ ያበራል (ላልቶ ሲነበብ) ምስጢርም እንደዚህ ትክዝዝ ይላል… ማዕጠንቱ ሳይደርሰው ውዳሴውም ሳያርሰው አንድ ማህሌት ተቁሟል… አንድ ማህሌት ተደርሷል..                             ---------------------------------------------- ፌስቡክ ላይ ላገኘሁት የኔው ትውልድ ትውልድ ሁሉ አቀርቅሯል፤ በምናብ አለም ውስጥ ሰጥሟል፤ በማይጓዝ የቅዠት መርከብ ሰፍሯል፤ በማያበስል እሳት ተጥዷል፤ በማይደርስ እቶን ይንፈቀፈቃል፤ ከወደቀበት ላይነሳ ቃል ሳይገባ ተገዝቷል፡፡ በጊዜው የጨፍልቅ ስልት፤ ይሄ ሁሉ ውሪ ባንድ ላይ ክትት፤ ይሄ ሁሉ ወፈሰማይ ሕዝብ ባንድ ቤት ስትት፤ ብሏል፡፡ ከወደቀበት ላይነሳ፤ቃል ሳይገባ እጅ ሰጥቷል፡፡ ትውልድ ሁሉ አጎንብሷል፤ በነጮች ጠልሰም የፍጥኝ ታስሯል፤ በትንንሽ የቅዠት መንደሮች ከትሟል፤ ባንድ ለጋ ወጣት ጥበብ እንደ ብራና ተወጥሯል፤ ከተኛበት ላይነሳ፤ቃል ሳይገባ ታማኝ ሆኗል፡፡ የጓዳ፣ የመንደሩን፣ የዘር ፣የማንዘሩን፣ ወሬ፣ክስ ፣ወቀሳ፣ አሉባልታ፣ ሮሮ፣ምሬት፣ጭቆና፣ሃሜታ፣ ፍቅር፣ሀዘን፣ውሸት፣ቅጥፈት፣ ሃቅ፣እውነት ፣እምነት፣ በምናብ እርሻ ሲዘራ፤ በምናብ እልፍኝ ሲታደም፣ሲያወራ፤ በዘመነኛ የጩኸት መንደር ተሰብስቧል፤