................‹‹አክተርና ድሃ››.................



እጅግ ረጅም ሰዓት ስለቆምኩና አማራጭ ስላጣሁ የመጣው ይምጣ ብዬ ተሳፈርኩባት፡፡ ጀልባ ላይ እንጂ ታክሲ ውስጥ መሆኔን የተጠራጠርኩት፤የሰማይ ስባሪ የሚወዳደራት አንዲት ሴት ወይዘሮ ገና ስትረግጣትና የታክሲዋ የጭንቀት ውዝዋዜ አንድ ሲሆን ነው፡፡ ባስ ብላ ደግሞ እኔው አጠገብ ስትቀመጥ የተሸከምኳት እንጂ ያስጠጋኋት አልመስልህ አለኝ... ይቅርታ ይደረግልኝና በመሠረቱ ይህን መሰል ሰው አጠገቤ ሲቀመጥ ምቾት አይሰጠኝም...ጸጉሩን 99 ዙር የጠቀለለ፣ያጥመዘመዘና ያልመዘመዘ ወጣት እንደባንዲራ ዝቅ ያለውን ‹ጅል ሱሪውን› እንደነገሩ ከፍ ለማድረግ እየሞከረ ጋቢናውን ሲይዝ ሹፌር መሆኑን አረጋገጥኩ...ይህ ግለሰብ ከዚህ በላይ ፀጉሩን ቢጠቀልል ወደፊት ተከርብቶ አደጋ ውስጥ ሊከተን እንደሚችል ገምቼ ብቻዬን ፈራሁ...
ታንኳ መሰል ታክሲ ውስጥ ያለሁ እስኪመስለኝ ድንገት እየተርገፈገፈች በመነሳት ጉዟችንን በግድ አስጀመረችው፡፡ ቀና ብዬ አሮጌ ቤተመቅደስ የሚመስለው ጋቢናዋን ስመለከት በጥቅሶች ተንቆጥቁጧል፡፡ አስገራሚው ነገር ታክሲዎቻችን ተሳፋሪዎቻቸውን በነገር ጎሸም ለማድረግ፣ለማስጠንቀቅ፣ፈገግ ለማሰኘት አንዳንዱ ደግሞ ለማስደነቅ አይንና አእምሮ የሚሸነቁጡ ጥቅሶችን ከላይ እስከታች ይደረድራሉ... ብዙ ጊዜ ግን ከማሳቅ ይልቅ ባለማሳቅ የሚያስቁ፣የሚያሳቅቁ እውነቶችን ሸክፈው የያዙ አባባሎችም ይበዛሉ... እናም ከጥቅሶቹ ውስጥ ደህና ነገር ካለ ብዬ ሳማትር አንዲት የተጎሳቆለች ጥቅስ ከነከነችኝ…
‹‹ደሃና አክተር ይንገላታል እንጂ አይሞትም!››
በሱቅ ሚዛን ይሁን በሕይወት ሚዛን ደሃና አክተር እኩል ሲመዘኑ አይቼ ስለማላውቅ የዚች ጎስቋላ ታክሲ ድፍረት አናደደኝ... እርሷ በእርግጥ ከየትኛው ወገን እንደሆነች አልተጠራጠርኩም ግን አጉል መንጠራራት አደረገችው...
እስቲ ፈጣሪ ያሳያቹ ደሃና አክተር እንዴት እኩል ይንገላታል? እኩልስ ቢንገላታ መጨረሻው እንዴት አንድ ይሆናል? ቢያንስ ‹‹እግዜር ያደለው ደሃ አክተር ይሆናል›› ተብሎ ቢስተካከል ምን አለበት? ደኃና አክተር ይቅርና ደሃ አክተር እንኳን ከደሃ ጋር እንዴት ይወዳደራል?
ባለፈው የምዕራባውያንን የጥናት ፁሑፍ ሳነብ አንድ አስገራሚ ነገር አገኘሁ፡፡ ከድህነት ወለል በታች ያለ እና ትክክለኛ ድሃ ልዩነታቸው ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ያትታል፡፡ ለነገሩ አሁን አሁን የሰጋሁት ይቺ ድሃ የምትባለውን ስምም ሊቀሙን ዳርዳር ማለታቸው ነው፡፡ በወረቀት ደረጃም እኛ ድህነታችንን ተቀምተን ከድህነት ወለል በታች ያለን እንደሆንን እነዚሁ ምዕራባዊያን መርዶውን አርድተውናል፡፡
እናሳ ብዬ ራሴን ስፋትሽ፡፡ ለካ ድሃ (standard poor) ለመባል ብዙ ነገር ይቀረኛል፡፡ አሁን ነው ማልቀስ አለ ያገሬ ሰው! ወደፊት ለልጆቻችን ታሪካችንን ስናወጋ ‹‹ድሮ ድሮ እንዴት ያለን ድሆች ነበርን መሰላችሁ፤የዛሬን አያርገውና ከድህነት ወለል በታች ከመውረዳችን በፊት በቀን 3 ጊዜ እንበላ ነበር›› እንል ይሆናል አልያም ምክር ቢጤ ጣል ስናደርግ ለልጆቻችን ‹‹ልጄ ተምረህ፣ጥረህ ግረህ ድሃ የመሆን ዕልምህን አሳካ›› እንል ይሆናል፡፡
ድሃ በህልሙ ቂቤ ባይጠጣ የምንላት አባባል አለችን ደግሞ፡፡ በእርግጥ ድሃ በህልሙ ቂቤ ባይጠጣ ምን እንደሚሆን ሁላችንም አንገምተው፡፡ ብቻ በአባባላችን እንረካለን፡፡
 በዚች ታክሲ ጥቅስ ደሞ ሹፌሩም፣ ወያላውም፣ ተሳፋሪውም፣ደሃውም ባይጽናና ምን ይኮን ነበር በሉኝ ምክንያቱም የዚች ጥቅስ አላማ ማጽናናት መሆኑ ነው እንደኔ ሆድ ለባሰው ደግሞ በተቃራኒው ንዴትን ትጭራለች...
ቅድም ጀምሮ ጸጉሩን ወደፊት ከመጠቅለሉ የተነሳ ወደፊት እንዳይከረበት የሚያሰጋው የመሰለኝ ሹፌር እኛንም ይዞን እንዳይከረበት በድጋሚ ብቻዬን ሰጋሁ ... በአንድ እጁ መሪውን እንጨበጠ በአንድ እጁ የገባለትን ጸጉር እየጠቀለለ ጎስቋላዋን መኪና አስፈሪው የእየሱስን ዳገት በጇ እይቧጠጠች እስክትወጣ ድረስ ነዳት... እኛንም ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከጎን ወደ ጎን.. እየናጠች፣ እያበራየች የዳገቱ ፍፃሜ ሆነ ...ውይ ምነው የሕይወት እንግልታችንም እንዲህ ቢፈፀም  በሕይወት ላይ አክተር ብንሆንባት ስል ተመኘሁ... ምኞት ብቻ ሆነ እንጂ...

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?