..............‹‹የፍየል ዘመን››...............



ልጆች እያለን አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣አያቶቻችን ስለ የዳቦ ዘመን፣የጥፋት ዘመን፣የበረዶ ዘመን፣ የድንጋይ ዘመን ያወጉን ተረቶች እውነት ቢሆኑ የሚገርመኝ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ይህን ለማመን ማረጋገጫ ያስፈልጋል፡፡ ግድም ነው፡፡ እኔ ግን ስለ ፍየል ዘመን ስነግራችሁ ምንም ውሸት እንደሌለው እናንተ ራሳችሁ ምስክር እንደምትሆኑን አምናለሁ፡፡ ‹‹ለምን?›› ብትሉ የኛ ዘመን የፍየል ዘመን እንደሆነ ብዙ ማረጋገጫዎች አሉኛ!
አንዱ ወዳጄ ከፍቅር ወዳጁ ጋር ሲያወጋ ፍቅር እንደያዘው ሳያቅማማ ነገራት ‹‹እኔም ፍቅር ይዞኛል ካንተ…ግን እኮ በፍየል ዘመን በግ አትሁን ይላል መፅሀፉ›› ስትል ከጣሪያ በላይ የሳቀችበት እውነት የገባው ዛሬ በአንዱ ተረኛ ስትለውጠው ነው
‹‹በእርግጥ እውነቷን ነው፡፡ በግ መሆን አልነበረብህም›› ስል እኔም በሳቅ እያውካካሁ ነገርኩት፤የገባው ግን አልመሰለኝም፤ድሮስ በግ እንዴት ይገባው!...
በፍየል ዘመን ሁሉም ነገር የከፋ ነው፡፡ በፍየል ዘመን ኑሮ ውድ ነው፣ በፍየል ዘመን ፍቅርን በገንዘብ መግዛት እንደሚቻል ማየት ችለናል፤በፍየል ዘመን ተኩላዎችና ፍየሎች ጎን ለጎን እኩል እየበሉ፣እየተባሉም ይኖራሉ፡፡
ማን ነው ይሔ የጥንቱ እንግሊዛዊ ደራሲ ስሙ ጠፋብኝ… እምምምም… ጆርጅ ኦርዌል ‹‹All animals are equal but some animals are more equal than others›› ብሎም የለ… እየየውም ሲዳላ ነው አሉ የኛ ጎረቤት፡፡ በፍየል ዘመን ሁሉም ፍየሎች እኩል ቢሆኑም (በጎቹንም ጨምሮ መሆኑ ነው) አንዳንድ ፍየሎች ግን ከሌሎች ፍየሎች በተሻለ እኩል መብት አላቸው፡፡ ነው ቁም ነገሩ፡፡
በፍየል ዘመን አራት እግር ያለው ወንድ ፍየል ሁልጊዜም ተጠቃሚ ነው፡፡ ቆነጃጅት ፍየሎችን በነጻ ከበጎች ነጥቆ ይወስዳል ምክንያቱም ‹‹በፍየል ዘመን በግ አትሁን›› ተብሎም የለ እንዴ?  ደግሞ እኮ…‹‹All animals are equal but some animals are more equal than others›› ይላል የፍየሎቹ መፅሐፍ፡፡ ይህች ፍየል ለፍቅር፣ ለገንዘብ፣ለትዳር ብላ በምትከፋፍላቸው የበግና የፍየል ወዳጆቿ ዘንድ እንደነገሰች ትኖራለች፡፡ ከእንቅልፉ የባነነ ፍየልም ይዞ ይጥላታል፡፡ ጊዜዋ ሲያልፍ ከበጎች ጎራ ለመቀላቀል ትራወጣለች፡፡ ወይ ዘመን!
በፍየል ዘመን የመጡ የበግ ለምድ ለባሽ ተኩላዎችም አሉ፡፡ ለየትኞቹ በጎች መብት እንደሚታገሉ ባይታወቅም፤ ብቻ  ለመብትህ፣ ለነፃነትህ እንታገልልሃለን የሚሉት መንጋ የበግ ዘር መስሏቸው እንጂ፤ ፍየል መሆኑን ቢያውቁት ኑሮማ እንዲህ ባልደከሙ፡፡ ለነገሩ ፍየሎቹም ያኔ ታግለው ነጻ ያወጡት የፍየል መንጋ ላይ ዛሬ ተኩላም ሆነውበት የለ እንዴ…? እነዚህስ ነገ ተኩላ አለመሆናቸውን በምን ማረጋገጥ እንችላለን?!
እናላችሁ እመኑኝ ያለንበት ዘመን የፍየል ዘመን ነው፡፡ ባታምኑኝም ተዉት ፤እናንተስ ከየትኛው ወገን እንደሆናችሁ ማን ያውቃል፡፡
‹‹በእንዲህ ያለ ዘመን አይተኙም ይነቋል፤
በላተኛው ሁሉ በያፋፉ ዘልቋል›› አለ አያቴ፤ ለካ ወዶም አይደል ነበር እንዲያ የመከረኝ፡፡ከበጎቹ ጎራ ሆኜ አልሰማሁትም ነበር እንጅ!

Comments

  1. :D ........''በፍየል ዘመን በግ አትሁን ይላል መፅሀፉ'' .... :) ..... ያምራል …ወድጄዋለሁ አባባሉን ….ዘመኑ,

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?