ቡና..ቡና


ልጅነትን ከሚያጣፍጡት እውነታዎች አንዱ ለነገሮች የምንሰጠው ልጅነታዊ እይታ ነው፡፡ መብላት፣ መጠጣት ፣መጫወት እንደምንም ብሎ ትምህርት ቤት አለመሄድ፤ በተለይ ነገ ትምህርት የለንም ወንዳታ! አቤት ደስ ሲል ፡፡ ልጅነት ደስ የሚል ጅልነትም ነው፡፡ ስለ ሒይወት የምንሰጠው ትርጉም፣ስለስነፍጥረት በራሳችን እውነት ነው ብለን የምንይዘው አቋም ወዘተ ልጅነትን እንድናፍቅ ያደርገኛል፡፡
ከልጅነት አሳዛኙና ቁጭትን የሚጭረው ነገር ቢኖር ልጆች እንደ ልጅ ተጫውተው፣ተጣልተው፣ተፋቅረው፣ሁሉን ነገር ሆነው ማደግ ያልቻሉ የያኔ አበባዎች የዛሬ ጎልማሶችና ወጣቶች ወይም አዛውንቶች ሕይወት ብቻ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ስለ እነዚህ አይነት ልጆች ወደፊት የሚለው ነገር ብዙ ቢኖረኝም ለዛሬ ግን አንድ ጥሩ ትውስታ ልጫርባችሁ፡፡ ይህ ትውስታ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻችሁ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ድሮ ድሮ ነው፡፡ ጧት ጧት፡፡ በተለይ ሰኞ ሰኞ ፡፡ ወደ ትምህርት ቤት መሔድ ከሚጠሉት ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ በተለይ ሀይስኩል ላይ ትልቁ ፈተናዬ ከአልጋዬ ላይ መውረድ ነው፡፡ እኔ ከአልጋዬ ላይ ከምወርድ ሀገር በአፍጢሟ ብትደፋ ይቀላል፡፡ ሁል ጊዜ ጧት ጧት ውዷ እናቴ ጋር ከባድ ጦርነት እንገጥማለን፡፡ ፋዘር በዚህ ሰጣ ገባ ውስጥ ጣልቃ ለለመግባት ይጥራል፡፡ እርሷ ዝም ባትለውም ገለልተኛ አካል ለመሆን ይጥራል፡፡
ጧት በተለይ ሰኞ ጧት ይህ የተለመደ የማዘርና የኔ ጦርነት ዛሬ ላይ ፈገግ ከሚያደርጉኝ ትዝታዎቼ ውስጥ ትልቁ ነው፡፡
የሁለት ሰዓት ዜና ተነቦ ሲጠናቀቅ ይህ የተለመደና አንዳች ሃይል ያለውን ዜማ ስሰማ ስቅቅ ይለኛል፤ ብቻ በእንቅልፍ ልቤ ሆኜ አዳምጠዋለሁ፡፡
‹‹የኢኮኖሚ ዋንጫ ቡና ቡና.
…………………….
አውዳ ነው ቡናችን ቡና ቡና››
ግጥሙን በደንብ አላስታሰውም፡፡
ይህ ዜማ ከሬድዮኑ ሲንቆረቆር ሰዓት መርፈዱን ያሳብቃል፡፡ ብቻ ይህን ዜማ ስሰማ በጣም እናደድ ነበር፡፡ ሁል ጊዜ በዚህ ዜማ ተመርኩዘው ይቀሰቅሱኛል፡፡ ንድድ እንዳለኝ ሳላበቃ እንቅልፌን በአይኔ ዘግኜ እንደያዝኩ፡፡
‹‹አንተ ልጅ ሁለት ሰዓት አለፈ እኮ አትነሳም?…ተነስ ጋድሚያ!›› ማዘር እንተቆጣች ወደ አልጋዬ ተንደርድራ ትመጣለች፡፡
እንደተጋደምኩ ‹‹እ..እ እሺ ››…….‹‹ትንሽ በናትሽ›› ከእንቅልፌ ጋር እንደታገልኩ በልምምጥና በንጭንጭ መንፈስ እለምናታለሁ፡፡ ዱላ ሳታነሳም ከራሴ ጋር እየታገልኩ እንቅልፌን ለመግታት እጥራለሁ፡፡
ወደ ፋዘር ዞር ትልና ‹‹ኸረ ተቆጣው ይህን ልጅ፡፡ ለምን ዝም ትለዋለህ ግን፡፡ እኔ ቆይ ብቻዬን አልቻልኩትም እኮ››
ፋዘር በሚያስፈራ ድምፅ ‹‹አንተ ልጅ አትነሳም እንዴ ትምህርቱን ተውከው?!››
ሬድዮናችን ማሳበቋን አታቆምም፡፡
‹‹ የታጠበ የይርጋ ጨፌ ቡና አንደኛ ደረጃ… በ300፣ ሺህ ብር ሲሸጥ…››
‹‹ያልታጠበ የጅማ ቡና……….››
‹‹ታጥቦ የተቀሸረ የቴፒ ቡና……….››  ከኢትዮጵያ ሬድዬ የሚሰማው የዕለቱ የቡና መሸጫ ዋጋ ዘወትር ጧት ጧት የእንቅልፍ መቀስቀሻ (አላርም) ነበረና ምርር አድርጌ እፈራው ነበር፡፡
ወይ ጊዜ ይገርማል፡፡ አይ! ጊዜ ነጉደ ሃይል፡፡ ዛሬ ግን ይህን ዜማ መስማት ይናፍቀኛል፡፡ ስንት ዘመን አለፈው መሰላችሁ፡፡ አሁን ግን ይህ ዜማ ይኖር ይሆን? የኢትዮጵያ ሬድዮን ከሰማሁ ዘመናት ስለተቆጠሩ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ በእርግጥ መቼም ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡


Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?