‹‹ስም ያለው ቀልብ የለው!››
ስም
ከስብ ይሸታል፣ስም ይወጣ ከቤት ይከተል ጎረቤት፣ ስምን ያወጣል መላዕክ፣ስም ያለው ቀልብ የለው… ወዘተ አማርኛችንን ካጥለቀለቁ
ትርጉም አዘል ምሳሌዎች መካከል እኛ ጦብያውያን ለስም የምንሠጠውን ከበድ ያለ ትኩረት የሚያንፀባርቁ አባባሎች ናቸው፡፡ ስምና ስያሜን
ስናነሳ እጅግ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን ማንሳታችን አይቀሬ ነውና ወጋችንን በአንድ ስፌት ብቻ እንመትረው ዘንድ በልጅነት ዘመኔ ከገጠሙኝ
አስቂኝ፣ የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክስ አይነት ገጠመኞቼ አንዱን መዘዝ አድርጌ ላጫውታችሁ፡፡
ጊዜውን
በውል ባላስታውሰውም ውቤ በረሃን የመሰለ ሰፈር ለቅቀን፣ ራስ አበበን የመሰለ ትምህርት ቤት ወደ ኋላ ትተን ወደ ዕድሜ ጠገቡ ፈረንሳይ
ለጋሲዎን የተሰደድንበት ጊዜ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ በጊዜው የ4ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርኩ አስታውሳለሁ፡፡ ቦታው ደግሞ ፈረንሳይን
ከቆሮቀሯት አንጋፋ ባላባትና የጦር አዝማች ራስ ስዮም፤ በስማቸው የተሰየመው የራስ ስዮም (ኋላ ላይ ደርግ ሕዝባዊ ሠራዊት ብሎ
የሰየመው) አሁንም ድረስ ፈረንሳይ ማዞርያ ያለው አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው፡፡
ለመጀመሪያ
ጊዜ በገባሁበት የሕዝባዊ ሠራዊት ት/ቤት ደስተኛ እንዳልነበርኩ በደንብ ትዝ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ከራስ አበበ አረጋይ ት/ቤት
የክፍል ጓደኞቼ ተለይቼ አዲስ ሰፈርና አዲስ ት/ቤት መግባት የተራራ ያህል ከብዶኝ ብል እውነት ነው፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ
የማደርገው ነገር ከልቤ እንዳልሆነ ያስታውቅብኛል፤በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ሳልፍ የሚከሰተው ይህ ባህሪዬ አሁንም ድረስ አብሮኝ እንደ
ዘለቀ ይሰማኛል፡፡
እናላችሁ
የከሰዓት ተማሪ በመሆኔም ከሰዓት በት/ቤቱ ግቢ ደርሼ አጭር የሰልፍ ላይ ዲስኩር ካዳመጥኩ በኋላ በአብዛኛው በቁመት ከሚበልጡኝ
4 ዲ ክፍል ተማሪዎች ፊት ተሰልፌ ወደ ክፍሌ ገባሁ፡፡ እዚህ ክፍል በመጨረሻው ዴስክ ረድፍ ተቀምጬ የአማርኛ ትምህርት ተማርኩ፡፡
የመጀመሪያውን የፈረንሳይ ሰፈር ትምህርቴን በዚህ ከጀመርኩ በኋላ መምህሯ ስም መጥራት ጀመረች፡፡ ስም ተጠርቶ ሲያልቅም የኔ ስም ባለመኖሩ እጄን አውጥቼ መምህሯን ጠየቅኩ፡፡መምህሯም ወረቀቷን አገላብጣ እዚህ ክፍል
እንዳልሆንኩ ነግራኝ ክፍሌን ፍለጋ ኮሪደር ለኮሪደር ስንገላወድ 4ኛ ኤ ክፍል ላይ ስሜ በሁለት ረድፍ ተፅፎ አገኘሁት በደስታ ወደ
ክፍሉ ገብቼ በአንድ ጥግ ላይ ቀጠን፣ጠየም እና ረዘም ከሚል ተማሪ አጠገብ ተቀመጥኩ፡፡ ቀጣዮ ክፍለ ጊዜ ሲጀምርም አጋጣሚ ሆኖ
ያቺው አማርኛ መምህር ገባች፡፡ ድንገት ስላየችኝ ክፍሌን እንዳገኘሁ ካረጋገጥኩላት በኋላ ድጋሚ ያንኑ ትምህርት መማር መጀመርኩ፡፡
እጅግ ከመሰላቸቴ የተነሳም ሳይታወቀኝ መረበሽ ጀምሬ ነበርና መምህርቷም በብስጭት ልትቀጣኝ ስለፈለገች
‹‹ስምህን
ንገረኝ!›› ስትል በቁጣ አንባረቀችብኝ
‹‹ዘመነ
ዮሐንስ›› መለስኩላት፤ ከጎኔ የተቀመጠው ተማሪ ድንገት ድንግጥ አለና
‹‹
እንዴ ቲቸር ውሸቱን ነው!›› በንዴት እኔን እያየ ሲናገር ምን ማለት እንደፈለገ ስላልገባኝ በመገረም ስመለከተው
‹‹
ሁለታችሁም ዝም በሉ አሁን!›› ድጋሚ ተቆጣች፡፡ ከጎኔ ያለው ተማሪ ግን ነገሩን ሊረሳው የቻለ አይመስልም፤ እኔ ደግሞ ተማሪው
ስሜን ሲሰማ ምን እንዳናደደው ስላልገባኝ በዝምታ አለፍኩት፡፡ ትምህርቱ ተጠናቆ መምህርቷ ስትወጣ ይኸው ተማሪ እንደነብር እምር
ብሎ ተነሳና
‹‹የማንን
ማርክ ለማቀነስ ነው አንተ!›› ብሎ ጉሮሮዬን አነቀኝ፤ግራ ገባኝ፡፡ ነገር ግን የዛሬን አያርገውና በልጅነቴ ራሴን መከላከል እችልበታለሁና
ቀልጠፍ ብዬ ዴስኩ ላይ በመውጣት እላዩ ላይ ተከምረኩበት፡፡
‹‹በለው፣
በለው፣በለው›› ከአንድ አቅጣጫ ሲሰማ፤ ከሌላ አቅጣጫ ደግሞ ‹‹እንትኑን ያዘው›› ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ እንዳትለቀው›› ድብድቡ ደመቀ
አጭርና ቀልጣፋ በመሆኔ ድብድብ ላይ በብዛት ተጠቃሚ እንደነበርኩም አስታውሳለሁ፡፡ እናም ከላይ ሆኜ ከስር በፍጥነቴ ተገርሞ ለመደብደብ
የተነሳሳው ተማሪ ድብደባዬን እየቀመሰ አልፎ አልፎም በመልሶ ማጥቃት የምሴን እያቀመሰኝ ድንገት የክፍሉ በር ተበረገደ፡፡ ቀጥሎም
ክፍሉ በፀጥታ ረጭ አለ፡፡ የሚደባደበኝም ልጅ ሆነ መላው ተማሪ በአንዴ እንዲህ በፍርሃት ያራዳቸው ምን እንደሆነ ለማየት ቀና ብዬ
ስመለከት አንድ መምህር ከፊታችን ወገቡን እንደያዘ ቆሞ አፈጠጠብን፡፡ መምህር ስዮም በመላው ት/ቤቱ በተጋራፊነቱና በምህረት የለሽነቱ
ይታወቃል፡፡
ሁለታችንም
አንጠልጥሎ ካነሳን በኋላ እያንባረቀብን፣ የጎማ አለንጋ እያወናጨፈብን፣ ከቆየ በኋላ ድንገት አዲስ ተማሪ መሆኔን መገንዘቡን በሚሳይ
የፊት ላይ ትርዒት ጥያቄ መጠየቅ ጀመረ
‹‹ምንድን
ነው የሚያደባድባችሁ?›› ሁለታችንም እኩል ማውራት ስንጀምር፤ ድጋሚ ተቆጥቶ
‹‹
አንተኛው ተናገር !›› አለ ወደ ባላንጣዬ እየጠቆመ
በፍርሃት
እየራደ ‹‹ ቅድም ረብሾ ቲቸር ስምህን ተናገር ስትለው የኔን ስም ተናግሮ አስመዘገበብኝ እና ቲቸር የኔን ስም ወስዳ ማርክ ልትቀንስብኝ
ነው›› ሲል
ግራ
እንደተጋባሁ ‹‹ እንዴ! ውሸቱን ነው!..እኔ የራሴን ስም ነው ያስመዘገብኩት››
‹‹ቲቸር
ማርያምን ካላመንከኝ ተማሪዎች ይጠየቁ›› አለ:: መምህሩም ወደ ተማሪዎቹ ዞሮ ሲጠይቅ፤ ተማሪዎቹ በአንድ ድምፅ ‹‹አዎ›› ሲሉ
መሰከሩብኝ፤ ንዴቴ ጨመረ፡፡
‹‹ያንተ
ስም ማነው?›› ሲል አፈጠጠብኝ መምህሩ፡፡ እኔም በድጋሚ
‹‹ዘመነ
ዮሐንስ›› አልኩ
ክፍሉ
ግራ በመጋባት ተንጫጫ፡፡ ባላንጣዬ ደግሞ አሁን ግራ የገባው ይመስላል ‹‹ እንዴ ቲቸር የኔ ስም ነው ዘመነ ዮሐንስ!›› እየተነጫነጨ
መናገር ጀመረ፡፡
መምህር
ስዮም ግራ የገባው ቢመስልም ድንገት ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ተራ በተራ እየደጋገመ ይጠይቀን ጀመር
‹‹ያንተ
ስም ማን ነው›› ሲለው ‹‹ ዘመነ ዮሐንስ›› መለሰለት ወደ እኔ ዞረና ያንተ ስም ማን ነው ሲለኝ ‹‹ ዘመነ ዮሐንስ›› መለስኩለት
፡፡ መምህር ስዮምና የክፍላችን ልጆች ነገሩ ቆይቶ ሲገባቸው መሳቅ ጀመሩ፡፡ እኔም ባላንጣዬም ነገሩ ሲገባን በግርምት መተያየት
ጀመርን፡፡
‹‹ዝም
በሉ!›› ሲል ተቆጣና ‹‹በሉ ከእንግዲህ በኋላ እንዳትጣሉ፡፡ የሁለታችሁም አንድ አይነት ስም እስከ እነ አባታችሁ መሆኑን መረዳት
ስላቃታችሁ ነው ይሄ ሁሉ ፀብ፡፡ በሉ ታረቁ ከእንግዲህ በኋላ በአያታችሁ ስም እንድትለዩ እናረጋለን›› በማለት መምህር ስዮም አስታርቆን
ከክፍል ወጣ፡፡
ከዛች
ዕለት ጀምሮ እኔና ሌላኛው ዘመነ ዮሐንስ በስማችን ብዙዎቹን ግራ እንጋዳባን እስከ 9ኛ ክፍል ቀጥለንም ነበር፡፡ የክፍል ጓደኞቻችን
ደግሞ እኔን ‹‹ትንሹ ዘመነ›› አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹ቀዮ ዘመነ›› እያሉ ሲጠሩኝ ያኛውን ዘመነ ደግሞ ‹‹ትልቁ ዘመነ›› እና
‹‹ጠይሙ ዘመነ›› እያሉ ይጠሩት እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ስም ያለው ቀልብ የለው ይሉትስ ይህ አይደል!?፡፡
የስሜ
መዘዝ በዚህ አያበቃም ጋዜጠኛ ከሆንኩ በኋላ በኔው ስም የሚጠራ ሌላ ጋዜጠኛ መኖሩንስ ምን ያህሎቻችሁ ታውቃላችሁ!ከእርሱ ጋርም
እንዲሁ አስገራሚ ገጠመኞች ዘና አርገው አልፈውኛል:: አወይ የኔ ነገር!
Comments
Post a Comment