ውሸት…ሲሸት
‹‹ወይ ውሸት››፣አቤት ውሸት ፣‹‹ሂድ ውሸታም›› ፣‹‹ወግጅ ቀጣፊ››
ውሸት… በቀድሞ የኣማርኛችን አገላለፅ ደግሞ ኩሸት… አልፎ አልፎ ቅጥፈት፣
ማታለል ሌላም ሌላም እንለዋልን፡፡ ለመሆኑ ምን ያህል ይዋሻሉ? ራስዎንስ
ከውሸታምነት አንፃር ምን ያህል ዋሾ እንደሆኑ አስበውትስ ያውቁታል?ከውሸት ያመለጠ ስብዕና ይኖርስ ይሆን? ጥናቶች ምን ያህሉ የዓለም
ሕዝብ ዋሾ እንደሆነ ሲጠቁሙ 60 በመቶው የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በ 10 ደቂቃ ውስጥ አንድ ውሸት ሳይቀባጥሩ እንደማያልፉ ስነግርዎ
ውሸቴን እንዳልሆነ ይረዱኛል ብዬ ተስፋ አረጋለሁ፡፡ ለነገሩ አጥኚዎቹስ ውሸታቸውን እንዳልሆነ ማን ማረጋገጥ ይችላል፡፡
ለመሆኑ ማን ነው የማይዋሸው? ሌላው ቢቀር ለእውነት ስንል እንዋሻለን
የምንልም አለን፡፡ በእርግጥ በእውነትና በውሸት መካከል ያለው የልዩነት ድንበር በብዙው የጠበበ ይመስላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እውነት
መራራና ድርቅ ያለ ሃቅ ነው፡፡ እውነት የሀሰትን ያህል የሚያማልል ገፅ ላይኖረውም ይችላል ስለዚህም ከእውነት ይልቅ ውሸት ብዙውን ጊዜ አማላይ ነው፡፡
ፈረንሳዊው ንጉስ ናፖሊዮን ‹‹ የዓለም ታሪክ ተስማምተው
የተቀበሉት ውሸት ማለት ነው›› ይላል፡፡ የታሪክ ሽሚያ ውስጥ እውነተኛው ነገርና መራራው ሃቅ ይካዳል ማለት ነው፡፡
ግራ አጋቢው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ ደግሞ ‹‹ የተበሳጨሁት ስለዋሸሀኝ አይደለም፤ ከዚያ በኋላ ምንም ስለማላምንህ
እንጂ›› ብሏል፡፡
ውሸት ከባድነቱ የቀጠፍነውን ቅጥፈት ሁልጊዜም ልናስታውሰው አለመቻላችን ነው፡፡ አብርሃም ሊንከንም ‹‹ማንም ሰው
በማስታወስ ብቃቱ ብቻ የተዋጣለት ውሸታም መሆን አይችልም›› ብሏል፡፡
ውሸታምን እንዴትስ ይለዩታል? ውሸትማ እኮ ይሸታል የሚል አንድ ወዳጅ አለኝ፡፡ ለመሆኑ ውሸት ይሸታልን ? ይኸው
ወዳጄ ከፍቅር ወዳጁ ጋር የተለያየሁት ውሸቷ ሸቶኝ ነበርም አለኝ፡፡ እርግጥ ሰዎች ሲዋሹ የሚታይ አካላዊ ምልክት ሊኖር ይችላል
ነገር ግን ውሸት ቅርጥፍ አድርጎ የለመደ/የለመደች ግን ውሸትን እንደውሃ በፊትዎ ሲያወራርድ/ስታወራርድብዎ ምንም ላይገባዎ ይችላል፡፡
ይህ ወዳጄ ሸተተኝ ያለውን የውሸት ሽታ ላካፍላችሁ፡፡
ወዳጄ ከአንዲት አቻ ኮረዳ መሳይ እንስት ጋር በፍቅር ክንፍ ያለበት የመጀመሪያ
ሳምንታት ውስጥ ነው፡፡ እንዲህ ሲል የሸተተተውን ውሸት አጫወተኝ፡፡
‹‹አንድ ቀን መገናኘት ባለመቻላችን ወደ ቤቴ አምሽቼ ስገባ ደወልኩላት፡፡››
‹‹እሺ ›› ለመስማት ከመጓጓቴ የተነሳ በየመሃሉ እንዲህ ማለቴ አልቀረም፡፡
‹‹ከዛልህ ስደውል ስልኳ ተይዞ ነበር፡፡ ድጋሚ ስደውልም ተይዟል፤አሁንም
እንደዛው ቆይቼም ስሞክር እንደተያዘ ነው፡፡ ብቻ ምን አለፋህ ለ1 ሰዓት ያህል ተይዞ ነበር›› አለኝ ፡፡ ትንፈሹን ሰብሰብ አደረገና
ቀጠለ፡፡
‹‹ምንድን ነው ግን ይህን ያህል የምታወራው፤ከማን ጋር ይሆን ስል ቅናት
ውስጤን እንደወረረው ወደ ቤቴ እየገባሁ ሳለ ድንገት መንገድ ላይ አገኘኋት እርሷም ወደ ቤቷ እየገባች ነበረ፡፡ የሚገርምህ ነገር
በአካል ሳገኛትም አሁንም ስልክ እያወራች ነው፤ ልክ እኔን ስታይ…››
‹‹በል ቻው እንደውም የምፈልገውን ሰው አገኘሁ አለች ከወዲያኛው ወገን
በስልክ ውስጥ ለሚያዋራት ሰው መልስ ሰጥታ፤መልስ እንኳን ሳትጠብቅ ወዲያው ዘጋችው፤ ገና ሳያት አወራሯ ጤነኛ አይመስልም››
‹‹እንዴት?›› ጠየቅኩት እንደተገረምኩ
‹‹በቃ ድምጿን ዝቅ አድርጋ፤ስሜት ውስጥ እንደገባች፤ ምስጥ ብላ ነበር
የምታወራው፡፡ ድንገት እኔን ስታይ ግን ፈጠን ፈጠን ብላ ማውራት ቀጠለች›› አለኝ
ወሬው ወዴት ሊያመራ እንደሚችል መገመት ቢከብደኝም ማዳመጤን ቀጠልኩ ጓጉቻለሁ፡፡
‹‹እና ስንገናኝ ምን ሆነሽ ነው ይህን ያህል ሰዓት ስልክ በሰላም ነው
ስላት አይ… እንትን ነው እኮ…ይሄ ስልክ ኢንተርናሽናል ስልክ ነው ለዛ ነው ከውጭ ተደውሎልኝ ነው፡፡ አለችኝ፡፡ እኔ ራሱ የማላውቀው
ስልክ ነው ስትለኝ በዝምታ አለፍኳት፡፡ እኔ ግን ነገሩ ስለከነከነኝ ወድያው አልተቀበልኳትም፡፡ ከዛ በኋላ አቅፌ ስስማት ራሱ ምንም
አልመሰላትም ነበር፡፡ አንድ ሰርፕራይዝ ወሬ ነግሬያት እንኳን አልደነቃትም፤አጠገቤ እንደሌለች ተሰማኝ፤ለረጅም ሰዓት ያወራችው ስልክ
የሆነ ቀልቧን ይዞት ሄዶ ነበር፡፡ ሴቶች ደግሞ እንዲህ ሲሆኑ ያስታውቅባቸዋል፡፡ እናም አንድ የሆነ ውሸት እንደዋሸችኝ ተሰማኝ››
ሲል
‹‹ምን ይሆን›› አልኩት
‹‹ለምን ዝም ብለህ አታዳምጥም ሺህ አመት አላወራ›› አለኝ ቆጣ እንዳለ
‹‹ እሺ ፣ቀጠል እሺ›› አልኩ ፈገግ
ብዬ
‹‹ ጥዋት አብረን ወደ ስራ በታክሲ ስንሄድ ስልኳን እየነካካች ሳለ ስለ
ማታው ስልክ እንደቀልድ አነሳሁባት፡፡ ከዛም ‹እኔ ራሱ ስልኩን አላውቀውም፤የማላውቀው ሰው ነው የደወለልኝ፤ኢንተርናሽናል ስልክ
ነው እያለች ስትደረድርብኝ ውስጤ ስላልተዋጠለት ሞባይሏ ላይ የምታሳየኝን ተደወለ የተባለውን ስልክ በቃሌ በፍጥነት እሷ ሳታስተውለኝ
ያዝኩት››
‹‹በመጨረሻም ቢሮ ገብቼ ኢትዮ ቴሌኮም ደውዬ ስልኩ አለም አቀፍ ስልክ
መሆን አለመሆኑን ጠየቅኩ፤ባለሙያውም ለምን ማወቅ እንደፈለግኩ ጠይቆኝ በተደጋጋሚ እየተደወለ ስላስቸገረኝ እንደሆነ አስረድቼ ትንሽ
ካስጠበቀኝ በኋላ ስልኩ በቅርብ ጊዜ የተለቀቀ የሃገር ውስጥ ስልክ እንደሆነ ነገረኝ፤ያኔ ድንግጥ አልኩኝ፤ውሸት ሸተተኝ፡፡ በቃ
ከዛ በኋላ እውነት ታውራ ውሸት መለየት አቃተኝ››
‹‹እና እውነቱን ሳትነግራት አለፍካት?››
‹‹አይ ከዚያ በኋላ ዝም ብዬ ማዳመጡን መረጥኩ››
‹‹ይገርማል›› ስል የወዳጄን ብሶት አዳምጬ አላለፍኩትም፤እሱም ማውራቱን
ቀጥሏል፡፡
‹‹እናልህ ከዛ በኋላ ነገሮች ብዙም ሳይቀጥሉ እውነትና ንጋት እያደር
ይጠራል እንዲሉ ሆነና ነገሮች ሲደራረቡ አስቀድሜ ራሴን በማግለል ራሴን ከውሸት ጥቃት አዳንኩ፤ብቻ ሁልጊዜ የምትሰጠኝ ምክንያት
ሁሉ ያስቁኝ ነበር ግን ለበጎ ነው፡፡›› ሲል በኩራት መንፈስ እየተነፈሰ ታሪኩን አወጋኝ፡፡
በእርግጥ ይገርማል፤ሰው ከዚህም በላይ ይዋሻል፡፡ውሸት እንደሚሸት ግን
የማውቀው ነገር ባይኖርም ይህ ወዳጄ ግን ውሸት እንደሚሸትው ይናገራል፡፡ በእርግጥ ግን ውሸት ይሸታል? ሸቷችሁስ ያውቅ ይሆን?
እናንተስ ምን ያህል ዋሾ ናችሁ፤መቼም ስለራሴ እንደማትጠይቁኝ ተስፋ እያደረግኩ ስለውሸትና ውሸታሞች የምትሉትን ትሉ ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡
Yeah ውሸት ይሸታል
ReplyDelete