ቡሼ ክፍል 2


ዛሬ ደግሞ ቡሼ እትዬ ማርኮኝ በራፍ ባለች ድድ ማስጫ ድንጋይ ላይ ጭቁን ብሎ እንደተቀመጠ እያቀለሰ ነው፡፡ ሲንሰቀሰቅ ወደታች የሚታገለውን ንፍጡን ወደ ውስጥ እየሳበ፤ሲለውም በእጁ እየገፋ ሲያስነካው ንብረቱ ከእጁ እንዳይወጣ የሚታገል የዘመኑን ነጋዴ ይመስላል፡፡ የሚያለቅሰውም ለዚህ መስሎኝ ነበር፡፡ ምን ሞኝ ነኝ ስል አሰብኩ፡፡
‹‹ምነው ቡሼ››  ጠጋ አልኩት፤ ቀና ብሎ እንኳን አላየኝም፤ፊቱን ወደአሊ ሱቅ አዙሮ የለቅሶውን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ በሚመስል ድምፅ በአዲስ ዜማ ያንበለብለው ቀጠል፡፡
ታናሽ ወንድሙ ጫጩ ከግቢያቸው እየሮጠ መጣ እና ጥያቄዬ እንደገባው ለማሳየት በሚመስል ፈገግታ ‹‹ልብሱ ላይ በእስኪብርቶ እየቸከቸከ...›› ሳያስጨርሰውና ለቅሶውን ሳያቋርጥ ቡሼ ያባርረው ጀመር፤ምስጢሩ እንዳይወጣበት ይመስላል፡፡
ትቻቸው ወደጉራንጉሩ ስዘልቅ የቡሼ ልብሶች ተሰጥተዋል፡፡ እነሱም በዝግታ ያልጠራ ውሃ ሲያንጠባጥቡ እንደቡሼ የሚያለቅሱ መሰለኝ፡፡ እነዚህ እንደበግ ቆዳ የለፉ ልብሶችን ዝቅ ብሎ ያላለፋቸው እግረኛ በግንባሩ ሳያብሳቸው አያልፍም፡፡ ዝቅ ያለ ዕድለ ቢስም ቢሆን ሳሙና የጠጣ የእብድ ምራቅ የሚያህል የውሃ ጠብታ ግንባሩን፣አልያም በራውን ሊያጠግቡት ይችላሉ፡፡
ትክ ብሎ ላያቸው የአንድን ሰው የተመሰቃቀለ የሕይወት ምዕራፎች ተሰቅለው እረፍት እያረጉ ይመስላሉ፡፡ ጠጋ ብዬ ሳስተውል ልብሶቹ ላይ እንደተባለውም የተሞነጫጨሩ ፁሑፎች ይታያሉ፡፡ ቆም ብዬ ስገረምማቸው ተደምረው ያላለቁ ቁጥሮች፣የማይገቡ ዓ/ነገሮች በተመሰቃቀለ አቅጣጫ ሰፍረዋል፡፡ እንደውም የተቦጨቀው ቲሸርቱ ላይ በተንጋደደ ፅሑፍ የተሳቀቁ ፊደሎች ‹‹ቃና ውስጤ ናዉ›› የተሳሳተ አጨራረስ በሚመስል ሰፍረዋል
‹ቡሼ ምን ነካው፤ከኛ ሰፈር ጩጬዎች ሁሉ ነቄው እሱ ነበር› ስል አሰብኩ ‹ያስገረፈችው ነገር እዚ ፁሑፍ ሳትሆን አትቀርም› ስል ግምቴን ሰነዘርኩ፡፡

ወደክፍሌ ሳመራም የቡሼ እና የጫጩ ስድድብና ድንጋይ ውርወራ ከርቀት እያጀበኝ ነበር፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?

ግብረ ሰዶማዊነት፤ሌላኛው ጋሬጣ