የኔ ትውልድ


‹‹አድናቂሽ ነኝ፤ መፅሔት ላይ አርፍሻለሁ›› አለኝ ያለምንም ሰላምታ፤የጅማ ቀረሮ ዛፍ የመሰለ ፀጉሩን በሁለት እጁ እያፍተለተለ፡፡ ወደፊት እንዳይከረበት ቢያሰጋኝም እሱ ወይ ፍንክች ጭራሽ ተጠጋኝ፡፡
‹‹እ..እኔን ነው?›› ሳያስጨርሰኝ ‹‹አንዳንዴ ዘጭ የምታረጊው ፊዚክስ ጸዴ ነው!›› አብሮት የቆመው ልጅ ደግሞ አቋረጠውና ‹‹ፊዚክስ በአማርኛ ግን አይከብድሽም?›› ጠየቀኝ ‹‹እ…›› ገና ለማውራት አፌን ስከፍት ዕድል አልሰጡኝም፤ ‹‹ኸረ ላሽ እንዴት ያቅታል አንተ ደሞ…›› የመጀመሪያው ልጅ ቀጠለ፡፡ ፊዚክስ በአማርኛ እዛው አፍንጫዬ ስር  ክርክር ጀመሩ፡፡ አጠገባቸው መቆሜን የረሱኝም መሰለኝ፡፡ ሁለተኛው ልጅ ወደኩ አልወደኩ እያለ የሚያስፈራራውን ጅል ሱሪ በአንድ እጁ ከፍ እያደረገ…
‹‹እኔ እምልሽ አሁን ግን እዛ መፅሔት ላይ አላይሽም፤ ላሽ አልሻቸው እንዴ…ወይስ አቀዘቀዙሽ›› ፈገግ ለማለት ሲሞክር የተሰነጣጠቀ መስታወት አስታወሰኝ፡፡
ግራ እንደገባኝ ‹‹አይ…›› ተናግሬ ሳልጨርስ ሌላኛው ተቀበለና  ‹‹ኸረ እንኳንም ቀረብሽ ከዚህ በኋላ የራስሽን ደቅ አርገሽ ይሔን ፒፕል መገንተር ነው››
‹‹ይኄን ፒፕልማ እንኳን ሳይንስ መድሃኔት ብትግተውም ገተታ ብቻ ነው!›› የመጀመሪያው ጨበሬ በቁጭት ያወራል፡፡ አሁን አስተውዬ ላያቸው ሞከርኩ፤የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይመስላሉ፡፡
እንዴ እንዴት ነው ነገሩ፤ እኔ ያልተሳተፍኩበት የራሴው ጉዳይ አፍንጫዬ ስር እየተወራ ምን ማድረግ አለብኝ፤ ምን እየተካሄደ ነው..ሆሆ.. ተገርሜ አልበቃኝም፡፡
ቀበቶውን የፈታ ሽማግሌ የመሰለ አሮጌ ታክሲ ሲመጣ  ተጋፍቼ፣ተገፍትሬ፣ተመትቼ፣ተረግጬ፣ተጨቁኜ ገባሁ፡፡
‹‹ኸረ ላሽ ያንቺን እማ ዛሬ እኛ ነን ዘጭ የምናረግልሽሽ›› አለኝ ሱሪው ጅል ልጅ እንዴ አብረውኝ ገብተዋል እንዴ..ገረመኝ፤ ከዚያች ደቂቃ በኋላ ሴት ሴት የሚል ነገር ተሰማኝ ‹‹አንተ›› ቢሉኝ አቤት ማለት ሊያቅተኝም ይችላል፡፡

እነዚህን ልጆች ከተለየሁባት ደቂቃ በኋላ ‹‹አንቺ›› …‹‹ስሚ›› ‹‹እናቱ›› ‹‹ቆንጂት›› የሚል ጥሪ በሰማሁ ቁጥር ለኔ እየመሰለኝ እደነብራለሁ፡፡ ፆታዬን አዛቡብኝ እኮ፤ በሰው ልጅ ፆታ እንዲህ ጢባጢቤ መጫወት እንደሚቻል በራሴ አየሁት፤ የእብድ ቀን አይመሽም አሉ እትዬ!

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?

ግብረ ሰዶማዊነት፤ሌላኛው ጋሬጣ