የሳውና ባዝ ትዝብቶች ክፍል 2


ዛሬ ገና ተሸነፍኩላችሁ፤ዛሬ ገና ተረታሁ (በሌላ ነገር እንዳትተረጉሙብኝ)፡፡ የሳውና ባዝ ቆይታዬን አንዱ አሻሽሎ ፉት አላት፡፡ ለነገሩ ይህን ያህል ሳውና ባዝ ውስጥ የሚቆይ ሰው እንዳለ አላውቅም ነበር፡፡ ሰውዬው ከሰመራ ነው የመጣሁት ሲልም የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ብቻ ‹‹ጥልቅ ሙቀት›› ውስጥ ቆይቶ ነው የመጣው (ያስታውቃላ)፡፡ቢሆንም ዶፒንግ ይመርመርልኝ፡፡  እኔ ግን እንደገባኝ ‹‹ጥልቅ እንትን›› ሳያስፈልገኝ አልቀርም፡፡
አስገራሚው ክስተት ደግሞ ከዚህ ይጀምራል-- እሳት በውሃ እየተቀቀልን ሳለ አንዱ ሰገጤ ተዝለፍልፎ ወረደ፤
‹‹መሬት ያዝ! መሬት ያዝ!›› ሁለት ወፋፍራም ወጣቶች አዘዙት
‹‹ኸረ መሬት ለኛም አልበቃም›› ሌላ አንድ-አይና ወጣት መለሰ በግማሽ ፊቱ እየሳቀ
‹‹መሬት ላራሹ!›› አንዱ ከሌላኛው ጥግ ጮኸ
‹‹የ67 ዛር ያለቀቀው አሁንም አለ! ፤ ልቀቅ ‹በእንትን› ስም›› ከተቃራኒ አቅጣጫ ጮኸ
ጫጫታው ቀጠለ፤ ስለ 67 አብዮት፤ ታህሳሱ ግርግር ሲወራ በመሐል የተዝለፈለፈው ሰገጤ ተረሳ!
ሁኔታው ያናደደው ፤ግማሽ ጡት ሰውዬ፤ በላብ የተንጨፈጨፈ አንድ አይኑን ገሎ፤በሌላኛው እንዳፈጠጠ ‹‹ኸረ ልጁ ፌንት ነቀለ! ልጁ ሞተ እኮ››
ወሬው ቆመና ሁሉም ወደወደቀው ልጅ እያየ፤ጫጫታው ሳይቋረጥ ሁለት ዛኒጋባ ቅርፅ ያላቸው ልጆች አፋፍሰው አወጡት፡፡
በኋላ ላይ በእሳት ተቀቅለን እንደወጣን፤ሻወር መውሰጃው ላይ ሰዎች እየተጨቃጨቁ ደረስኩ፤ ሻወር ገብቶ አልወጣም ያለ፤ነፍሰጡር የመሰለ ወጣት ጋር ነበር ንትርኩ፡፡
‹‹ባባ ለቅለቅ ብለሽ ልቀቂልን፤ጥልቅ ሻወር አልተባለም እኮ››
‹‹አልወጣም!››
‹‹ኸረ ፈጣጣ! ለምን?››
‹‹እኛ ሰፈር ውሃ ከጠፋች…›› ሰይጨርሰው እየሳቅን ተውነው፤
‹‹በፌስታል ይዘሽ ላጥ ነዋ፤መጨረሻ ላይ›› ያንዱ ምክር መሆኑ ነው፡፡
ከቆይታ በኋላ …የ4ኪሎ ሰፈር ልጅ የሚመስል አንድ ወጣት ‹‹ ቪክስ ሊጨመር ነው ግቡ!››  መቀመጨውን እየፈተገ ተጣራ፣
ጀርባውን እንደሆዱ የሚጠቀም  ነፍሰ ቀጭን ልጅ ደሞ ፤የሚኒስቴር በሚመስል ድምጽ  ‹‹ቪትዝ ሊሰጠን ነው !?›› (ሊቀልድ ሞከረ)
ድጋሚ እሳት ውስጥ እንደገባን ቪክሱን በግሌ ከቱርክ ነው ያመጣሁት ያለ አንድ ፊኛ ሆድ ሰውዬ ጉራውን እየነፋብን ፤ቪክሱን እሳት ውስጥ ከመጨመሩ ሁላችንም ተዝለፈለፍን፤
‹‹እውነትም ቪክሱ የቱርክ ነው!›› ሁሉም የተስማማ ይመስላል
‹‹እና እኛ የቻይና ነን! እንዲህ መቋቋም ያቃተን›› የተቆጨ ጎልማሳ ማጅራቱን ሲፈትግ ላየው፤ጀርባው በደንብ ያልተጠረገ ጥቁር ሰሌዳን ያስታውሰዋል፡፡ስለቻይና መወራት ተጀመረ፡፡ በመሐል ቪክሱ ተረሳ፡፡
ከእሳት ጫጫታ እንደወጣሁ በር ላይ ሌላ ልጅ ‹‹ አባ መታሻ ያስፈልግሻል!?›› … ቀኑን ሙሉ ስፈትግ ያመሸሁት አይታየውም እንዴ?! በባልጩት መፈተግ እኮ ነው የቀረኝ!! አፈጠጥኩበት፡፡ እስኪ እየኝ ልለው ፈለኩ እና ተውኩት ! ያሳዝናል፤ያናድዳል፡፡ ለሞራሌ እንኳን…መታጠቤን ቢገምት…



Comments

Post a Comment

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?

ግብረ ሰዶማዊነት፤ሌላኛው ጋሬጣ