እትዬ የሺና ሳንጃው!


‹‹አዬ የዘለዳው አንተው ሁናቸው እንጂ እነዚህስ እንኳን ሰው መኪናም አይገፋቸው›› አሉ እትዬ የሺ::
ገርበብ ባለው በራቸው ፊት ለፊት እንደ አፈጉባኤ ጉብ እንዳሉ ከፊታቸው የተደረደረውን ሲኒ እና ጀበና ያስተካክላሉ፡፡ አንዴ ከፊታቸው የተሰለፈውን የእጣን ማጨሻ ቆስቆስ ያደርጋሉ፤ አንዴ ደግሞ ከሚንጫጫው ቴሌቪዝናቸው ጋር ለረጅም ደቂቃዎች ይፋጠጣሉ ፡፡ገርበብ ብሎ ከተከፈተው በራቸው ተረክ ባለ ድባብ ወደ ውጭ የሚንቦለቦለው እጣን ደግሞ ማንንም መንገደኛ ይጣራል፡፡
ከእትዬ የሺ በስተሰሜን ባለች በርጩማ ቁጭ ብለው ቡናቸውን ማግ እያደረጉ አይናቸውን ከቴሌቪዢኑ ሳይነቅሉ ‹‹አ..አቀብለው››…‹‹ ኸረ? ኸረ በለው?...ኤድያ!›› የሚሉት ደግሞ የአቶ ማንተጋፍቶት ባለቤት ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ስማቸው ስለሚጠፋኝ በባለቤታቸው አስታክኬ ነው የምጠራቸው ሁልጊዜም የሚገርመኝ ነገር ተመሳሳይ ሃገራዊ ጉዳይ ሲኖር በተለይም በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ሲኖር የሰፈራችን አሮጊቶች ተሰባስበው ቡናቸውን እየጠጡ ሲከታተሉ ማየት የተለመደ ነው
አንዳንድ የሰፈራችን ልጆች ደግሞ እትዬ የሺም ሆኑ እነዚህ ጎረቤቶቻቸው በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ በተለይ እግር ኳስና እሩጫ ላይ ያላቸው አቋም መንግስት በጂቲፒው ላይ ካለው አቋም ይስተካከላል ይላሉ፡፡
ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከማሊው ስታደ ደ ማሊ ክለብ ጋር የሚያደርገውን ግጥሚያ ደግሞ አንድ ላይ በሕብረት እየተከታተሉ ነው፡፡
ጥሎብኝ እኔ ደግሞ እንዲህ ሕዝብ አይኑን፣ልቡንና ቀልቡን ሰቅሎ የሚይዝ ሃገራዊ ጉዳይ ከመከታተል ይልቅ የሚከታተለውን ወፈሰማይ ሕዝብ ማየት ያዝናናኛል፡፡
‹‹አዬ እንደው ዛሬስ ብዙ ሳይገባባቸው….›› እትዬ ልኬለሽ መናገር ሲጀምሩ ‹‹ምነው አንቺ ደግሞ፤ ኤጭ አታሟርቺባቸው!›› ቆጣ ብለው መልስ ሰጡ እትዬ የሺ
‹‹ አይ አንቺ ደግሞ እኔስ ምን አልኩና?!..ገና ሳልናገር?›› እትዬ ልኬለሽ ቡናቸውን በቄንጥ እንደያዙ ፈጠን ብለው ቅሬታቸውን አሰሙ
አየር ለመውሰድ በማሰብ ግቢያችንን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ምን አይነት የተለየ አየር እንደምወስድ ባይገባኝም ዞር ዞር ማለት ስጀመር የመንደራችን መንገዶች ጭርታ የምፅዓት ቀን ላይ እንጂ የእረፍት ቀን መሆኑን እንደተጠራጠርኩ ተረዳሁ
ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ወደ ቤት ስመለስ አካባቢያችን በጩሀት ታወከች፡፡
‹‹ሳንጃው ሳንጃው!›› የሚል ጩሀት ስሰማ ጸብ የተነሳ መስሎኝ ደነገጥኩ!
ፈጠን ብዬ ግቢ ገብቼ ስመለከት በደስታ ባሕር ተውጠው የሚጮሁት ለካ እትዬ የሺ ናቸው፡፡
እንዲህ አልኩ ለራሴም ‹‹ወይ እትዬ የሺ ይህ የኳስ ፍቅራቸው አንድ ቀን ከመንደራችን ወጣቶች ጋር ዲኤስ ቲቪ ቤት ሳያሰልፋቸው አይቀርም››
ያኔ ደግሞ ምን እንደሚሉ ገመትኩ ‹‹ማንቼ! ማንቼ!››

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?