እንደወረደ አንድ ለመንገድ... ከወልቂጤ እስከ ጅማ


ጥሎብኝ አገር ማየት እወዳለሁ፡፡ ይህ አባዜዬም በዚች ትንሽ አገር ላይ ታች ያዞረኛል፡፡መቼም እንደብዙዎቹ ፀሐፍቶች የጉዞ ማስታወሻ የመቀመር ብቃትም ፍላጎትም ባይኖረኝም እግረ መንገዴን ግን የገረመኝን ነገር እንካችሁ ከማለት ወደኋላ አልልም፡፡እና ይህ አባዜዬ ከጓደኞቼ ገንጠል አርጎኝ በህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ውስጥ ከተተኝ፡፡እስከ ጅማ ድረስም በዚህ መልኩ ልጓዝ ወሰንኩ፡፡
እናላችሁ ጫት እንደባሕር ዛፍ በሚሸመጥጥባት ወልቂጤ ከተማ ስንደርስ መንገደኛው ሁሉ እንደቆሎ ሸጎጥ እያረገ የሚገባው መኪና ይቁጠረውና ዙርባ ዙርባውን የወልቂጤ ጫት ተሸክመው በመስኮት ላይ የሚያፈጡብዎ ትንንሽ ነጋዴዎች ደንበኞቻቸውን የሚያውቁ ይመስል መንገደኛውን እየለዩ ይጎተጉታሉ፡፡
ወደ ጅማ የሚጓዘው መንገደኛ ሁሉ ያልቃመ ኬላ ላይ ይያዛል የተባለ ይመስል ሁሉም በርብርብ ይገዛል፡፡ የገረመኝ ትዕይንት ደግሞ ዘግየት ብሎ መጣ፡፡ የጅማ እንስቶች ለቂማ ያላቸው ትጋት ፈገግ አሰኘኝ፡፡ እናም ከፊትለፊቴ በሚታየኝ ወገን ቁጭ ያለች አንዲት እመጫት የግራ ጡቷን የልጇ አፍ ውስጥ ሰድራ ቀኝ ጉንጯን ተርዚና እንደወጠረው እያመነዠከች ከወንድ ቃሚ ባልደረቦቿ ጋር በወሬ ትንጫጫለች፡፡ እንግዲህ ልጅም ምርቃናው በናት ጡት ወተት መልክ እንደሚደርሰው እያሰብኩ በፈገግታ ዙርያ ገባን መቃኘት ቀጠልኩ፡፡
ከሰዓታት በኋላ...
ወፈ ቃሚ በሙሉ ቡዝዝ ባለ ዓይን ከፊት ለፊቱ የሚመዘዘውን መንገድ እየተመለከተና ከፊት ለፊቱ የሚምዘገዘገውን የጊቤ በረሃ እየገላመጠ፤ያለ አግባብ ባዱ አፉን እያላመጠ፣እያኘከ በምርቃና ቁዘማ ውስጥ በፀጥታ ተቀምጧል፡፡ የመረቀነውን ካልመረቀነው መለየት የሚቻለውም በፈጠጡና በቦዘዙ ዓይኖች መጠን ሳይሆን አይቀርም መሰለኝ የአንዳንዱ አይን ከሽፋሽፍቱ ወጥቶ በመኪናው እንቅስቃሴ የሚወዛወዝ ይመስላል፡፡... መቃም ባህላዊ አመጣጥ ያዳበረው በሃገራችን ብቻ ባይሆንም የኛ ሁኔታ ግን ለተመልካቹ ያዝናናል፡፡
ጅማ መድረሱን የተመለከተውም መንገደኛውም ከምርቃናው ድባብ ወጥቶ ለመውረድ ዝግጅቱን በጫጫታ ያጅበዋል፡፡ ጅማም ቃሚዎቿን እጇን ዘርግታ መቀበል የምታቀውቅበት ይመስል እዚህም ሌላ ትዕይንት እያየሁ ለመውረድ ተዘጋጀሁ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?