ርዕስ አልባ ግጥሞች
ዝምምም…ባለ ዝምታ
ስጥምምም..ባለ ፀጥታ
አንድ ገጽ አለ…
የልብ ድቢ የሚያስመታ
ከእርጋታው ፊት ለፊት
ትክዝዝ… ካለው ሽፋሽፍት
አንድ ገጽ አለ…
ልብ የሚያሸፍት
ከፀዓዳው ጉንጭ፤ከጸዓዳው
ከንፈር ስር
አንድ ማህሌታይ አለ
የሚንዠረዠር
ሳይጻፍ ሳይነገር…
ዝምታም እንዲህ ይፈሳል..
ማቀርቀርም እንዲህ ይወርዳል…
ትካዜም እንዲህ ያበራል
(ላልቶ ሲነበብ)
ምስጢርም እንደዚህ ትክዝዝ
ይላል…
ማዕጠንቱ ሳይደርሰው
ውዳሴውም ሳያርሰው
አንድ ማህሌት ተቁሟል…
አንድ ማህሌት ተደርሷል..
----------------------------------------------
ፌስቡክ ላይ ላገኘሁት የኔው ትውልድ
ትውልድ ሁሉ አቀርቅሯል፤
በምናብ አለም ውስጥ
ሰጥሟል፤
በማይጓዝ የቅዠት መርከብ
ሰፍሯል፤
በማያበስል እሳት ተጥዷል፤
በማይደርስ እቶን ይንፈቀፈቃል፤
ከወደቀበት ላይነሳ ቃል
ሳይገባ ተገዝቷል፡፡
በጊዜው የጨፍልቅ ስልት፤
ይሄ ሁሉ ውሪ ባንድ
ላይ ክትት፤
ይሄ ሁሉ ወፈሰማይ ሕዝብ
ባንድ ቤት ስትት፤
ብሏል፡፡
ከወደቀበት ላይነሳ፤ቃል
ሳይገባ እጅ ሰጥቷል፡፡
ትውልድ ሁሉ አጎንብሷል፤
በነጮች ጠልሰም የፍጥኝ
ታስሯል፤
በትንንሽ የቅዠት መንደሮች
ከትሟል፤
ባንድ ለጋ ወጣት ጥበብ
እንደ ብራና ተወጥሯል፤
ከተኛበት ላይነሳ፤ቃል
ሳይገባ ታማኝ ሆኗል፡፡
የጓዳ፣ የመንደሩን፣
የዘር ፣የማንዘሩን፣
ወሬ፣ክስ ፣ወቀሳ፣ አሉባልታ፣
ሮሮ፣ምሬት፣ጭቆና፣ሃሜታ፣
ፍቅር፣ሀዘን፣ውሸት፣ቅጥፈት፣
ሃቅ፣እውነት ፣እምነት፣
በምናብ እርሻ ሲዘራ፤
በምናብ እልፍኝ ሲታደም፣ሲያወራ፤
በዘመነኛ የጩኸት መንደር
ተሰብስቧል፤
ትውልድ ሁሉ አቀርቅሯል፤
ትውልድ ሁሉ በእውን
ሞቷል፤
ከሰዋዊ ሕይወቱ፤ባርነቱን
መርጧል፤
ለራሱ ላይሆን፤ላይኖር
ምሏል፤
የባዳ ኑሮ ሊያደምቅ
አንገቱን አቀርቅሯል፡፡
አ.አ የካቲት 23
2008
Comments
Post a Comment