ጥያቄ አለኝ


በእውነቱ ወንደኝነት ያጠቃናል፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ‹‹ወንደኝነት››የሚል የአማርኛ የቃል አረባብ ባይኖርም፤ያራባሁት እኔው ነኝ፡፡በቤተ ሙከራዬ፡፡ አብዛኞቹ የአማርኛ ቃላት

አላግባብ ፀሐይ ላይ
በመዋላቸው የተነሳ ያልባከነ ቃል ስላጠረኝ እንደሆነ ብቻ ተረዱልኝ፡፡ በእውነቱ እኛ ወንዶችም ሆንን አንዳንድ ሴቶች ወንደኝነት(ፆተኝነት) ያጠቃናል፡፡
ለምን ብትሉኝ፤እህ ብትሉኝ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ስንቶቻችን ነን የሴት አያቶቻችንን ስም የምናውቅ?ባባት በሚጠራ ማህበረሰብ ውስጥ እስኪ የአያቶችህን ስም ጥራ/ጥሪ ብንባል…
‹‹ጉልማ፣ዳንዴው-ዳንዴው፣ሃይሌ-ሃይሌ-ሴሬቦ…›› በቃ ወንድ አያቶቻችን ብቻ፤ ሴት አያቶቻችንንስ? የእናትህ እናትስ? የአባትህ እናትስ? በሴት አያቶቼ ስም እምላለሁ ከአንድ በላይ የእናቱንና የአባቱን እናት፣እናት፣የእናት እናት፣የእናት እናት እናት የሚያውቅ ካለ እኔ እቀጣለሁ፡፡ ታላላቅ ስብዕናን የተጎናፀፉ ሴት አያቶቻችን እንደዋዛ ስማቸው ይጠፋል፡፡ በእውነቱ ወንደኝነት ያጠቃናል፡፡
በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በወንድ የበላይነት የምትጦዘው ዓለም የሰው ልጅ ወንደኝነት የሚያጠቃው ብቸኛ እንሰሳ ይመስላል፡፡ለምን ብትሉ ይኄ በአንዳንድ እንሰሳት አይሠራማ!፡፡ ለምሳሌ በማህበረጅብ ዋነኛ መሬ ሴት ጅብ ናት፡፡ ወንድ ጅብ የበይ ተመልካች ነው፡፡ ጅብ እንኳን በእንስቶች ይመራል! ይህንንስ ምን ያህሎቻችን እናውቃለን?
አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ ከዛሬ 10ሺህ ዓመታት በፊት እነ ግሪክ ሳይሰለጥኑ የነበረው የሰው ልጅ ታሪክ ነው፡፡የዛሬን አያርገውና አለም ያኔ በሴቶች ትመራ ነበር፡፡ ቢቢሲ እንኳን ተደንቆ ይህን ታሪክ <<When God was a woman>> ሲል ተርኮታል፡፡
የዛሬን አያርገውና አለም ያኔ በሴቶች ስትመራ፤አማልክቶች፣ጣኦታት ሁሉ ሴቶች ነበሩ፡፡ፈጣሪ ሳይቀር ሴት ነው ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ማህበረሰቡን ደግሞ የሚያስተዳድሩት እንስቶች ነበሩ፡፡የጦር መሪዎች፣አገር አስተዳዳሪዎች፣ከተማ ጠበቂዎች… ሁሉም በእንስቶች የተያዘ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ወንዶች ከቤት ውስጥ ባልነትና የእንስቶች አገልጋይነት ውጭ ምንም ሚና የላቸውም ማለት ነው፡፡ እኔ ስጠረጥር ደግሞ ወንዶች የቤት ሥራ ሃላፊነት ጫና ነበረባቸው፡፡ ከጊዜ በኋላ ወንዶች ብዙ ነገር ነቄ ሲሉ ሁሉም ነገር ተገላቢጦሽ ሆነ አሉ፡፡ ይህ ታሪክ ለምን ተደብቆ ኖረ እንዳትሉኝ ምክንያቱም ወንደኝነት ስለሚያጠቃን ነው፡፡
በነገራችን ላይ በዚያ ዘመን ልማታዊ ሚዲያ ቢኖር ምን እያለ ማህበረሰቡን ሊያስተምርና፣ሊሰብክ እንደሚችል አስባችሁታል?
‹‹ወንዶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት ይቁም!››
‹‹ ወንድን ልጅ ማስተማር አገርን እንደማስተማር ይቆጠራል!››
‹‹ወንዶች ልዩ ድጋፍ ያሻቸዋል!››
‹‹ወንዶች ያለዕድሜያቸው እንዲያረግዙ..›› ውይ ለካ ወንዶችን አይመለከትም ይኼኛው መፈክር
ምናልባት ‹‹ወንዶች ያለዕድሜያቸው እንዲያስረግዙን ማድረግ ወንጀል ነው!››
ይላል ብዬ እጠረጥራለሁ፡፡ እናንተስ?

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?