Elusive creative genius

ስለቃሉ የቀረበ ትርጓሜ ምን ማለት እንደምችል ባላውቅም እንደ ርዕስ የተጠቀምኩት ቃል ‹‹ቅዠታዊ ልህቅና›› ከምንለው የአእምሮ ብቃት ጋር አንድነት አለው፡፡ እንዲህ ያሉ ቅዠታም ግን ባለ ልዕለ ሃያል አእምሮ ባለቤቶችና የፈጠራ ሥራ ልሂቃን መኖራቸውን ሳይንስ በየጊዜው ይነግረናል፡፡ በእርግጥ እንዲህ ያሉ ሰዎች በሁሉም ሞያ ቢኖሩም በኪነጥበቡ ውስጥ ያሉት ግን ለየት ይላሉ ይለናል ኒውሮ ሳይንስ፡፡
ነገሩን ወደራሴው ሞያ ፀሐፍትነት ለውሰደውና፤ሁሉም ሰው ፀሐፍት መሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ሰው ደራሲ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድን ጥበበኛ ከሌላ የሚለየው ግን የተሰጥኦው ውጤት ነው፡፡ ይህ ተሰጥኦ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ይመስላል፡፡ እነዚህ ጥቂቶች ደግሞ ቅዠታዊ ልህቅናን የተጎናፀፉ ይሏቸዋል፡፡
ከታሪክ መዝገብ ሲመነዘር ጥንታዊ ሮማውያንና ግሪካውያን ፀሐፍት አንዳች መንፈስ ያረፈባቸው ናቸው ይባላሉ፡፡ እነዚህ ፀሐፍት ከተራው ጸሐፍት ይለያሉ፤ሶቅራጠስ ራሱ ሳይቀር ‹‹ዲመን›› ‹‹አንዳች መንፈስ ››በላዬ ላይ ሆኖ በል በል ሲለኝ ሃሳቦቼን አፈልቃለሁ፡፡ እነዚህ ሃሳቦቼ ደግሞ ከሌላው ግዜ የተለዩ ናቸው፡፡ ጠብ እንኳን አይሉም›› ብሏል፡፡
ለነገሩ እኚህ ታላላቅ ፀሐፍት እንደ ተራው ፀሐፍት በየጊዜው ለምን አይፅፉም፤እንደ ዳኛቸው ያሉ ፀሐፍት ለምን በየጊዜው በአደፍርስ አያጠምቁንም? እነ ሐዲስ አለማየሁ ሁልጊዜ ያን የመሰለ ነገር መፃፍ ለምን አቃታቸውስ? ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡ የጥበብ ሰዓታት ‹‹moments of creativity›› ዝም ብሎ እንደውሃ ዥረት አይመጣም፡፡ ያቺ ሰዓት መቼ እንደሆነች ጥቂት ጥበበኞች ያውቋታል፡፡ አንዳንድ ልሒቃን ሲጋራውን ሲያቦኑ፣በመጠጥ ጠርሙስ ውስጥ ሲንቦራጨቁ፣ሲቅሙ አልያም ፅፁን ሲጋቱ ድንገት የፈጠራ ሥራ ፍልቅ ትልላቸዋለች፡፡ እንደነሱ አገላለፅ፡፡ ኤልሳቤት ጊልበርት የ‹‹ኢት ፕሬይ ላቭ›› ደራሲ ወፈፌ ከሚባሉት ፀሐፍት አንዷ ናት፡፡ እንዴት እንደምትፅፍ ስትናገርም፤‹‹ድንገት በይ በይ ሲለኝ›› ትላለች፡፡ በአንድ ወቅት መኪና እያሽከረከረች ድንገት የመጣላትን ሐሳብ መፃፍ የማትችልበት ቦታ በመሆኗ ወደ ሰማይ ቀና ብላ እያየች ‹‹አብደሃል እንዴ! መኪና እየነዳሁ እኮ ነው!?›› በማለት በይ በይ እያለ ሐሳብ የሚያፈልቅላትን መንፈስ እንደተቆጣችው በሳቅ ተውጣ ተናግራለች፡፡
እነዚህ እውነተኛ ፀሐፍት ፈጠራቸውን የሚቀሽሩበት መነሻ ክስተት (ሙዲ ሲሆኑ) በል በል ሲላቸው ነው፡፡ ከዘልማድ የአስተሳሰብ ድንበር አልፈው በራሳቸው የአስተሳሰብ ጉዞ እንደ ሕዋው ተለጥጠው የዘለቁ ናቸው ይባላልም፡፡ በኛው አገርም ለዚሁ ምሳሌ የሚሆን ቅዠታዊ ልህቅናን የተላበሰ ፀሐፊ ልታገኙ ትችላላችሁ፡፡ እንደኔ ምሳሌ ደግሞ ዳኛቸው ወርቁን እንውሰድ፡፡ ለብዙዎቻቹ የዚህ ደራሲ ትውስታ የሚሆን አንድ መፅሐፍ አለ፡፡ አደፍርስ፡፡ ዳኛቸው አደፍርስን መሞነጫጨር የጀመረው እንዲህ በል በል ሲለው እንደሆነ በአንድ የትውስታ ፁሑፍ ላይ እንዳነበብሁ ትዝ ይለኛል፡፡ ኋላ ላይ በዚያች የቅዠት ቅፅበት የሞነጫጨራት ፅሑፍ አቅሉ ሲመለስለት እርሱ ለራሱ አንብቦ ሊረዳው ባለመቻሉ ቀድዶ ጣለው፡፡ ከጣለበት አንስቶ ያነበበው ወዳጁ ደግሞ አንዳች ሃይል በዚያች ፁሑፍ ውስጥ በማየቱ ‹‹ይሄማ እብድ የሆነ ፁሑፍ ነው!›› ሲል እንዲቀጥለው አበረታታው፡፡ ይኸውና አደፍርስም ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ ጥቂቶች ብቻ አንብበው ሊረዱለት ችለዋል፡፡በጊዜውም ቢሆን ለዚህ ትውልድ እንዲህ ያለ ፁሑፍ አይገባውም ያሉም ነበሩ፡፡
አንዳንድ እንዲህ ያሉ ፀሐፍትን ከተራ ፀሐፍት የሚለያቸው ድንበር ይህ ነው፡፡ ከራሳቸው የምቾት መስመር ወጥተው ማሰብ ችለዋል፡፡ ፈጥረዋል፡፡ እንዲህ ስል ደግሞ ሌሎቻቹ መፃፍ አትችሉም ማለቴም አይደል እንደው ለጨዋታ ያህል ነው እንጂ፤እናንተ ባትኖሩ ፌስቡክንስ ማን ያደምቀው ነበር!? እውነት ነው ኑሩልን ፀሐፍያን!
ጎንደር- ጳጉሜ 2007

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?