ሰላማዊ እንቅልፍን ይሻሉ?

እንግዲያውስ የእንቅልፍዎ ጠንሳሽ ሆርሞኖችንባህሪያት ሊያውቁ ይገባል

ሜዲካል መፅሔት መስከረም 2008

 ሰው ሆኖ የማይተኛ የለም፡፡ መተኛት ስል እንቅልፍ ብቻ መሆኑን እንዲታሰብልኝ፤እንሰሳም ሆኖ እንደዛው፤የተለየ አፈጠጣር ካላቸው በስተቀር፡፡ እንቅልፍ ለሰው ልጅ አካላዊ ዑደት ወሳኝ ተፈጥሯዊ ክሰተት መሆኑ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ሳይንስ ስለእንቅልፍ የሚረዳው እውነታ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ቢመጣም እስካሁን ያልተመለሱ አያሌ ጥያቄዎች አሁንም እንዳሉ ናቸው፡፡ እንቅልፍና ሕልምን የሚያያይዘው ምስጢር ደግሞ ዋነኛው ነው፡፡ ለምን እንደምናልም ዛሬ ድረስ ግልፅ መልስ የለም፡፡ ሕልም ትርጉም አልባ ወይስ በሕይወታችን ውስጥ ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ይሆን የሚለውም ጥያቄ እንዲሁ እንቆቅልሽ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እንቅልፍ በሕይወታችን ውስጥ ስላለው ወሳኝ ድርሻ ሳይንስ ብዙ የሚለን ይኖራል፡፡ እንቅልፍና የሰው ልጅ አካላዊ ንቃት፤ሥራ እና አጠቃላይ ኡደት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ እንቅልፍን የሚያህል ታላቅ የጡዘት ምስጢር የሚጠነስሱ አካላዊ ሆርሞኖች ደግሞ ሌሎቹ ባለሚናዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሆርሞኖችን ማወቅ መረዳትና የሚጠብቁብንን መፈፀም በአግባቡ ለመተኛትና ጤነኛ ውጤታማ ሕይወት ለመምራት የሚያስችለንን ስንቅ እንደያዝን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡
በሰውነታችን ያሉ ሆሮሞኖች በአጠቃላይ የሰውነታችንን የሥራ ክንዋኔ የሚቆጣጠሩና የሚፈፅሙ ናቸው፡፡ በአጭሩ ኬሚካላዊ መልዕክት ልንላቸው እንችላለን፡፡ወደ አንድ የሰውነታችን ክፍል አልያም ሕዋስ የሚልኩት የኬሚካል መልዕክት ጠብ አይልም፡፡በተፈለገው ጊዜ ውስጥ ይፈፀማል፡፡ በአብዛኛው በእኛነታችን ላይ ሃያልነት አላቸው፡፡
ከዚህ ቀደም እንደሚገለፀውም፤በእድገታችን፤በሜታቦሊዝም ስርዓታችን፤በመራቢያ አካላትና ስሜታችን ዙሪያ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የሆርሞኖቻችን መሆኑ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያም በላይ በእንቅልፋችን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሆርሞኖችም አሉ፡፡ የእነዚህን ሆርሞኖች ተግባር፣ባህሪና ፍላጎት ጠንቅቀን ከተረዳን እንደ አመላቸው ልንይዛቸው እንችላለን፡፡

የለሌት ዘበኞች?

በእንቅልፍ ሰዓት ብዙ አይነት ሆርሞኖች በሰውነታችን ይመነጫሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ጌርሊንና ሌፕቲን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ሆርሞኖች የምግብ ፍላጎታችን ላይ ሚና አላቸው፡፡ ብዙ እንቅልፍ እጦት ያለባቸው የምግብ ፍላጎታቸው ቢዛባ ሰዎች እነዚህ ሆርሞኖች ሥራቸውን ባለማከናወናቸው መሆኑ ልንዘነጋው አይገባም፡፡ በእንቅልፍ ላይ ሳለን ዕድገታችንንና አካላዊ ጥገና የሚያካሂዱ ሆርሞኖች ይመነጫሉ፡፡ ይህ አዋቂዎችንም ይመለከታል፡፡
ኢንሱሊንና ኮርቲሶል የተሰኙ ሌሎች አካላዊ ኬሚካሎች ደግሞ በእንቅልፍ ወቅት መጠናቸው ይመዘናል፡፡ እነዚህ ሆርሞኖች ተመጣጣኝ ሲሆኑ ከእንቅልፋችን እንደነቃን ይርበናል፡፡ የምግብ ፍላጎታችንን ጤናማ ያደርጉታል፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሆሮሞኖች ሥራ ስንል በአግባቡ እንቅልፋችንን ልንተኛ ግድ ነው፡፡
ሌላኛው አስገራሚ የሆርሞኖች ሥራ ቢኖር ከእንቅልፋችን በሽንት አልያም በሌላ ተፈጥሯዊ ጥሪ እንዳንነቃ የሚሰሩት ሥራ ነው፡፡ አልዶ ስቴሮንና አንቲዲዩሬቲክ ሆርሞኖች የዚህ ሥራ ሃላፊዎች ናቸው፡፡ ሕጻናት እነዚህ ሆርሞኖች ገና ባለመብዛታቸው የተነሳ አልጋቸው ላይ እንደተኙ ሽንታቸው ሊያመልጣቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ በአዋቂዎች ላይ እንዳይከሰት እነዚህ ሆርሞኖች ነቅተው ይጠብቃሉ፡፡

አካላዊ ሰዓት- ‹‹እንቅልፍህ መጣ፤እንቅልፍ በቃህ››

ሆርሞኖች አካላዊው ሰዓታችንን ይቆጣጠራሉ፡፡ሲመሽ እንቅልፋችን እንዲመጣ፤ሲነጋም እንዲበቃን የሚያደርጉ ሆርሞኖች አሉ፡፡ የመጀመሪያውና እንቅልፋችን እንዲመጣ ለማድረግ በሰውነታችን የሚመነጨው ሜላቶኒን የተሰኘው ሆርሞን ነው፡፡ የሚላቶኒንን ባህሪና ፍላጎት ከተረዳን እንቅልፋችንን ማንም አይከለክለንም፡፡ ብርሃናማ ቦታ እንድተኛ አይፈቅድልንም፡፡ለምን ቢባል ሜላቶኒን በአግባቡ አይመነጭም፡፡በማታ ሥራቸውን የሚያከናውኑ ግለሰቦች ቀን ቀን መተኛት የሚያዳግታቸውም ለዚህ ነው፡፡ ሜላቶኒን ለመመንጨት አይናችን ከብርሃናማ ቦታ መራቅ ይኖርበታል፡፡ አልያም ጨለማ ክፍል ውስጥ ብንተኛ ሜላቶኒን በአግባቡ ስለሚመነጭ በቀላሉ መተኛት እንችላለን፡፡
አርቴፊሻል ሜላቶኒን በክኒን መልኩ እየተዘጋጀ ገበያ ላይ ውሏል ነገር ግን የአወሳሰዱ ጉዳይ የሐኪም እርዳታ ያስፈልጋልና ከመውሰዳችን በፊት ሐኪሞቻችንን ብናማክር የተሻለ ይሆናል፡፡

ወንዶች፤ሴቶች-የወሲብ ሆርሞኖችና እንቅልፍ

ከሁሉም ከሁሉም በተለየ መልኩ ሴቶችን በተመለከተ የሜላቶኒን ተጽዕኖ እስከ የወር አበባ ዑደት ድረስ የዘለቀ ተፅዕኖ አለው፡፡ በሴቶች ላይ የወር አበባ ከመታየቱ በፊት የሚከሰቱ የሆርሞኖን ለውጦች፤ፕሮጄስትሮንን ጨምሮ ማለት ነው፤የሰውነታቸውን የሙቀት መጠን ይቀይረዋል፡፡ይህ ደግሞ በተያያዥ መልኩ በቀላሉ ወደ እንቅልፍ እንዳይገቡ ያደርጋቸዋል፡፡የቅድመ የወር አበባ ስሜቶች ጠንካራ መሆን በሴቶች እንቅልፍ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፤ይህም በቀን ከማንቀላፋት እስከ በሌሊት ፍጥጥ ማለት ድረስ ይደርሳል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ በእርግዝና ወቅት ሊጠነክር ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ያለአግባብ እንቅልፍን አለመተኛት ወንዶች ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ያደርሳል፡፡ የወሲብ ሆርሞን የምንላቸው የወንዶች ቴስቶስትሮን በእንቅልፍ ጊዜ ብቻ ይመነጫሉ፡፡ ወንዶች በቂ የቴስቴስትሮን መጠን ማመንጨት ከፈለጋችሁ በትንሹ ሦስት ሰዓታትን መተኛት ይጠበቅባችኋል፡፡ እንደ አግባቡ ከሆነ ደግሞ ከ6 እስከ 8 ሰዓታት መተኛት በቂ የሆነ የወሲብ ሆርሞንና የዘር ፍሬ ምርት በሰውነታችሁ እንዲፈጠር ጊዜ ይሰጣል ማለት ነው፡፡ እናም ስለእንቅልፋችን ልንጠነቀቅና ችላ ላንል ይገባል፡፡
በዘልማድ የተነሳ በአኗኗር ዘይቤያችን መሠረት እንቅልፍ ልናጣ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ አድሬናሊን የተሰኘው ሆርሞን እንቅልፍ እንዳንተኛ እና ንቁ ሆነን እንድናድር ያደርገናል፡፡ ይህ ሆርሞን በመደናገጣችን አልያም በተፈጠረብን ውጥረት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ ሆርሞን በተፈጠረበት ሰዓት አካላችን ይዝላል እንጂ እንቅልፍ የሚባል ነገር በአይናችን አይዞርም፡፡ለምሳሌ የተዛባ እንቅልፍ መተኛት ከፍተኛ መጠን ያለው ፋት ክምችት በሆዳችን ላይ እንዲፈጠርና ወደቦርጭነት እንዲቀየር አስተዋፅዖ አለው ፡፡
እንቅልፍና ሕልም፤እነዚህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የሆኑ የተፈጥሮ ክስተቶች ኦክሲቶሲንና ኮርቲሶል የተሰኙ ሆርሞኖች መጠን መብዛት ወይም ማነስ የሕልማችንን ይዘት ይወስኑታል፡፡ እነዚህ ሆርሞኖች አስፈሪ አልያም አስደሳች ነገሮችን በህልማችን እንድናይ ወሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ ነገር ግን ለምን የሚለው ጥያቄ አሁንም እንቆቅልሽ ነው፡፡
የኮርቲሶል ሆርሞን መጨመር ደግሞ በሌላ መልኩ እንቅልፍ እንዳንተኛ ያደርገናል፡፡

ኮርቲሶል እንዴት በሰውነታችን ውስጥ መጠኑ ሲጨምር፤እንቅልፍ ስናጣም፤

v  በሽታ የመከላከል አቅማችን ይቀንሳል፣
v  የማስታወስ ብቃታችን ይቀንሳል፣
v  የሆዳችን መጨነቅና በምግብ ቶሎ ቶሎ ይወጠራል፣
v  ቦርጭና የወገብ ውፍረት ይከሰታል፣
v  የዕድገት፣የቴስቴስትሮን፣የኦስትሮጅን ሆርሞኖች ባግባቡ አይመነጩም፣

የኮርቲሶል መጠንዎ በሰውነትዎ ቀንሶ፤ሰላማዊ እንቅልፍ እንዲተኙ እነዚህን ይተግብሩ፤

v  ማታ ማታ ቲቪ ይቀንሱ፤ቢችሉ አይጠቀሙ፤በተቃራኒው መፅሐፍት ያንብቡ፤አእምሯዊ ሥራዎች በፍጥነት ወደ እንቅልፍ እንድንገባ ያደርጉናልና፣
v  የቤትዎ መብራት ደማቅ ነው፤እንግዲያውስ እንቅልፍ ሊተኙ ሲያስቡ ደብዛዛ ብርሃን ይጠቀሙ፤ምክንያቱም እጅግ በደመቀ ብርሃን ውስጥ ትንሽዬዋ የኢንዶክራይን እጢ ሜላቶኒንን ማመንጨት ያቅታታል፤እናም መተኛት አይችሉም፣
v  ከሙዚቃ ዘና የሚያደርግ ሙዚቃ ያዳምጡ፣
v  እንቅልፍ ካጡ ሞቅ ያለ ሻወር ይውሰዱ፣
v  አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የገላ ቅባት መጠቀም ይኖርብዎታል፣
v  የእግር ማሳጅ ይውሰዱ፤በተለይ በተቃራኒ ፆታ የሚሰጥ የእግር ማሳጅ ሰውነታችን ዘና እንዲልና ሜላቶኒን እንዲመነጭ ይረዳናል፣ኮቲሶል በሰውነታችን ከፍተኛ ሲሆን የደም ዝውውራችን ይረጋል፤የእግር ማሳጅ አልያም ሪፍሎክሶሎጂ የደም ዝውውራችንን ያፋጥናል፣
v  በተለይ ሕጻናት ማታ ማታ ሙቅ ሻወር ወስደው የእግር ማሳጅ ቢሰጣቸው እንቅልፋቸው ጤናማ ይሆናል፣
v  በዕለት ውሎህ ውስጥ ስላደረግኻቸው መልካም ነገሮች አስበህ ደስተኛ ሆነህ ወደ አልጋህ ሂድ፤ይህ ዘዴ ብዙ የስነልቦና ባለሙያዎች የሚመክሩት ነው
መልካም እንቅልፍ!

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?