‹‹እንኳን በደህና መጡ፤ወደ ሰፈራችን እየገቡ ነውና ዝቅ ብለው ይብረሩ››
ይህን
የመሰለ የመልካም ምኞት ሰሌዳ ከመግቢያው ላይ ባያንጠለጥልም ወደኛ ሰፈር የመጣ እንግዳ ወይም ቱሪስት አልያም ፀጉረ ልውጥ ፤ በድሆች
ማህበራዊ መስተጋር ሊደመም ይችላል፡፡ የዛሬን አያርገውና ድሃ ደልቶት የሚኖርበት፣ የዛሬን አያርገውና ሰክሮ እርስ በእርስ የሚፈረካከስበት፣
የዛሬን አያርገውና ሚስትና ባል የሚወሽሙበት፣የሚወሻሸሙበት ሰፈር ነበር፡፡ የኛን ሰፈር ከእርስዎ ሰፈር ለየት የሚያደርገውን የቱሪስት
መስህቦቹን ካላወቁ እኔ ትንሽ ልጠቋቁምዎ፡፡
አያርገውና
የገቡበት ሰፈር የማያውቁት ከሆነና ግራ ከገባዎ እኛ ሰፈር ደርሰው ይሆናልና አንዳንድ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችን ሊያስተውሉ ይችላሉ፡፡
ግር እንዳይልዎ አሁንም እነዚህን ነገሮች በደንብ ያጢኑ፡፡
ገና
ታክሲ ከመያዥያው፣ከባስ መጠበቂያው ስፍራ ‹እምቢኝ፤ አልሰለፍም› ያለ ወፈ ሰማይ ሕዝብ ካዩ ለታላቁ ሽኩቻ ራስዎን ያዘጋጁ፡፡ ሴቶቹ
አይጋፉም ብለው ካሰቡ ተሳስተዋልና ነቃ ይበሉ፡፡ ነፍሰ ጡር ናትና ብለው ከተሳቀቁም ተሳስተዋል፡፡ ይህን የግፊያና ሽኩቻ ትዕይንት
ተሳታፊ ሆነው በድል ከተወጡ ወደኛ ሰፈር እየሄዱ እንደሆነ አይጠራጠሩ፡፡
በገቡበት
ታክሲ ውስጥ ጆሮዎን ከሚከታትፉ የከተፋ ቤት ዘፈኖች ጋር እየተደናቆሩ እንዲሄዱ ከተፈረድብዎ በእርግጥም ወደኛ ሰፈር እየመጡ ነውና
ቅር አይበልዎ፡፡ እንደውም ጥቂት ዘፈኖችን በተደጋጋሚ እንዲሰሙ ከተገደዱ የኛ ሰፈር ታክሲ ውስጥ ነዎት ማለት ነው፡፡
ወገብ
ከሚይዝ ተራራ ጋር መኪናዋ ግብ ግብ ከገጠመች በእርግጥም ወደኛ ሰፈር እየገቡ ነውና የወንበርዎን ቀበቶ ጠበቅ ያርጉ፤ታክሲ ውስጥ
ከሆኑ ደግሞ የሱሪዎን ቀበቶ ያጥብቁ ምክንያቱም እነዚህ ሁለት አቀበቶች በየቀኑ የሆሊውድ አስፈሪ ፊልሞችን የሚያስንቁ አደጋዎች
ያለምንም ቀረፃ የሚያስተናግዱና እርስ በእርስ መጨራርስ ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ለተቀረው የዓለም ሕዝብ የሚያሳዩ፤ የሰፈራችን
ሾፋሪዎች ደግሞ መኪና መንዳት እንደማይችሉ ያስፎገሩ ናቸው፡፡ ይህን ጊዜ እንደየእምነትዎ መፀለይ ብቻ ነው የሚችሉት፤እምነት ከሌለዎት
ደግሞ በሳይንሱ የአትራክሽን ህግ ብቻ የመፅናናት ዕድል አለዎት፡፡
‹‹እናትህን
እንት ትሁንና ሂሳብ እኮ ነው የምልህ!››፣‹‹እንትን ላርግህ፣የናትህ መኪና መሰለህ እንዴ!›› ወዘተርፈ በመሰሉ ሃረጎች ነገር
ከጀመረዎት ፣በትህትና እያናገሩት ጠብ ያለሽ በዳቦ የሚል የታክሲ ረዳት ከገጠመዎ፤ ያለምንም ጥርጥር የኛ ሰፈር ልጅ ነው፤ አልያም
በኛ ሰፈር በኩል አልፏል፤ወይም ወዳጆቹ የኛ ሰፍር ልጆች ናቸው፡፡ እናም የተሸነፉ መስለው ማሳለፍ ነው እንጂ ሹፌሩም ተደርቦ ይሄንኑ
ስድብ ሊያከናንብዎና ካልመታዎት ብሎ መጋበዙ ስለማይቀር ቢቀርብዎት እመርጣለሁ፡፡
በእግርዎ
ጠባብዋን የሰፈራችንን አስፓልት እየሄዱ ነው እንበል፤ በየእርምጃዎ አስር ቆጥረው ዞር ሲሉ አንዳንድ ታሪክ ቀመስ ጠጅ ቤቶችን ካገኙ
በእውነቱ የኛን ሰፈር እየጎበኙ መሆን አለበት፡፡ አጠቃላይ ቆጠራ ተካሂዶም የነዚህ ጠጅ ቤቶች ብዛት ከነዋሪው ቁጥር ጋር እንደሚስተካከል
ማዕከላዊ ስታስቲክስ በአንድ ወቅት ጠቁሞም ነበር አሉ፡፡ ይህ ታድያ አንጋፋውንና በአዲስ አበባ ካሉ ጠጅ ቤቶች በዕድሜ የሚስተካከለው
እንደሌለ ማዕከሉ የገመተው ወርቁ ጠጅ ቤትን ጨምሮም ነው፡፡
አሁንም
በየአቅጣጫዎ እያማተሩ እንደ ዛፍ አልፎ አልፎ ተተክለው በሚያገኟቸው ግሮሰሪዎችና መጠጥ ቤቶች ብዛት ተደምመው ሳያበቁ፤ይባስ ብሎ
ለአይን ማረፊያ እንኳን አንድም ካፌ ካጡ እኛ ሰፈር ገብተዋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መጠጥ ቤት እንጂ ካፌ እኛ ሰፈር የሚያከስር
ሥራ ነውና፡፡ ካላመኑኝ በየመጠጥና ጠጅ ቤቱ መጠጥና እንክርዳድ ፍቅርን የሚከመኩሙ የሰፈራችንን ወጣቶች ይጠይቁ፡፡
በየመንገዱ
ዳር በጥዋቱና በምሽቱ መግቢያ ልክ እንደ አዕዋፍት ብቅ ይላሉ፤ከአላፊው አግዳሚው መኪና ጋር ግብ ግብ ሊገጥሙም ይችላሉ፡፡ እነዚህ
ፍጡራን ሰክረው ሥርዓቱን የሚሳደቡ የድሮ ጠጪዎች ናቸው፡፡ ድንገትም ሊገጥሙዎ ይችላሉ ፤ሰክረው ራሳቸውንና ፈጣሪን የሚሳደቡ ወጣቶች
ጋር ከተገጣጠሙ ደግሞ ግር እንዳይልዎት የኛ ሰፈር ወሳኝ የንጋትና ምሽት አብሳሪ ፍጡራን ናቸውና፡፡
እንደ
ማሳ ተክል ተቃቅፈው የበቀሉ ደሳሳ ቤቶች ውስጥ ለውስጥ እየገቡ ቢሆንና መውጫው ቢጠፋዎ ነውጠኛው 11 ቀበሌ ውስጥ ነዎት ማለት
ነው፡፡ እንደውም እዚህ ቀበሌ ጥቂት ቀናት የማደር ዕድል ቢያገኙ ከአዛን ቀድሞ የሞት ጥሪ ጥሩምባ ያነቃዎ ነበር፡፡ በየቀኑ ሰው
እንደ ቅጠል እየረገፈ ነገር ግን የነዋሪ ቁጥር ካልቀነሰብዎም አሁንም 11 ቀበሌ መሆንዎን አይዘንጉ፡፡ ምስጢሩ ምንድን ነው ብለው
አይጠይቁ፤ አንዳች ሃይል ሊሆን ይችላልና፤እንደውም ይህን ሰፈር ለማፍረስና ሪል ስቴት ለማድረግ ተነሳስቶ የነበረው ኤርሚያስ አመልጋ
የደረሰበትን ኪሳራና ስደት አስበው እርስዎም ዝም ፤ጭጭ ይበሉ፡፡
እጅግ
ብዙ ሕፃናት በተለይ ደግሞ መልካቸው የሚመሳሰል ውስጥ ውስጥ ባሉ መንገዶች እየተጯጯሁ ሲጫወቱ ካዩ እንዳይደነቁ የኛ ሰፈር ሕፃናት
እንደ እርስዎ ሰፈር ልጆች አባቶቻቸው የማይታወቁ እንዳይመስልዎ፤የብዙ የሰፈራችን ኮረዳዎችና የጥቂት ወንዶች ውጤት ናቸው፡፡
ወደ
አንዱ ግሮሰሪ ዘው ብለው ገቡ እንበል፤ልጆቻቸውን ሰብስበው መጠጥ ቤት የከተሙ ወላጆችን ካዩ ያለምንም ጥርጥር እኛ ሰፈር ተወልደው
ያደጉ ወላጆች ናቸው፡፡ የእኛ ሰፈር መጠጥ ቤቶች ልጆቻቸውን ሰብስበው በምሽት ‹ክተት ቤተሰብ› የሚሉ ወፈፌዎች የበዛበት ነውና
አይደመሙ፡፡
አንዲት
ኮረዳን ጠበሱ እንበልና ለትዳር ቢያበቋት ‹‹ማርያምን ያለ ቬሎማ ከቤቴ አልወጣልህም›› ካለችዎ የኛ ሰፈር ልጅ ናትና አለቀልዎት
ማለት ነው፡፡ ያለዎት አማራጭም የሰፈርዋን ኮረዶች ለማስቀናት ፈልጋ እንደሆነ በመረዳት ከእርሷ ጋር መስማማት አለብዎት፤አለበለዚያ
ለሰፈርዋ ልጅ ያለ ቬሎ እንዲጠቀልላት አሳልፈው እንደሰጡዋት ይቁጠሩት፡፡
እንደውም
በኛ ቤት መግቢያ በኩል በሚገኙ ድርብርብ ድንጋዮች ላይ ተደራርበው የተቀመጡ ወጣት መሰል ሰዎች ከገጠሟችሁ አንገታችሁን ደፍታችሁ
ማለፍ ነው አልያ አዲስና እውቅና ያልተሰጣቸው ተረቦች፣ለከፋዎችና ስድቦች በእርስዎ ላይ ተሞክረው ውጤታማነታቸው ይገመገምብዎታልና፡፡
ምን
ይህ ብቻ የኛን ሰፈር ልዩ ያደርገዋል መሰልዎ፤ሳምንቱን ሙሉ ስለመብራት መጥፈትና ውሃ እጥረት ከሰሙ እኛ ሰፈር ገብተዋልና ሰፈር
ቢቀይሩ ነው የሚያዋጣዎ፡፡
በቴሌቪዥን
መስኮት የሚያዮዋቸውን (የባለቀለምና የብላክ ኤንድ ሁዋይት ዘመን) ጀማሪ እና የቆዩ አርቲስቶች፣አቀንቃኞች ወይም ሌሎች ሰዎች ዳቦና
እንጀራ ለመግዛት በየሱቁ ውርውር ሲሉ ማየት የሚያዝናናዎ ነገር ሊሆን ይችላልና ወደኛ ሰፈር ብቅ ይበሉ፡፡ መቼስ እኛም ባቅማችን
የምናስጎበኘው ዝነኛ አለን!.. ‹‹ኡኡቴ ድንቄም ዝና!›› አሉ እማማ እታፈራሁ!
በነገራችን
ላይ እማማ እታፈራሁን ካዩ ደግሞ የኛ ቤት አካባቢ ደርሰዋልና አደገኛ ዎሾች ስላሉ ልክ እንደ ሰፈር ልጅ ‹‹አክት›› እያደጉ ይለፉ፤ ፀጉረ ልውጥነትዎ ከታወቀ የእማማ እታፈራሁ ውሾች
ከበባ እና ጥቃት አስጊ ነው፡፡
ብቻ
እርስዎ ወደኛ ሰፈር ይምጡ እንጂ ከእነዚህ የበለጡ የሚጎበኙ ነገሮች አያጡም፡፡ የኛ ሰፈርና ዕድገት የሚሉት መንፈስ አንገት ለአንገት
ተናንቀው መሸናነፍ አቅቷቸው ስንት ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ ሮም ባንድ ምሽት ባትገነባም 22ን የመሰሉ ውቅሮዎች ባንድ ምሽት ተገንብተዋል
ነገር ግን የኛን ሰፈር ባንድ ጀንበር ለማፈራረስ ማሰብ ምንኛ ጅልኛ ነው እናንተዬ!? ብቸኛው የድሃ ማቆያው መንደራችን እኮ ለቅርስነት
መቆየት አለበት፡፡ አይመስላችሁም!?
Comments
Post a Comment