የሳውና ባዝ ትዝብቶች ክፍል-3

ከዚህ ዘመናዊ ምድጃ ሥር በሚያፍን ሙቀት ውስጥ በላብ፣በውሃ፣በእንትን ታጥቤ እየተዝረበረብኩ ነው የተሰማኝን፣ ያየሁትን የማጫውታችሁ፡፡ከጊዜያዊው ስቱድዮ፡፡ለነገሩ እሳት ውስጥ ቋሚ ስቱድዮማ እንዴት ይታሰባል፡፡ መቼስ ያው በዓልም አይደል የኛ ቤት..(ይቅርታ የመንግስት ፍልውሃ) ግርግር ይበዛዋል፡፡ ለበዓል ንፅህናችንን ለመጠበቅ የምንፈፅመውን ተጋድሎ ሌላም ጊዜ ብንሞክረው ኑሮ…ዛሬ ግን ቶሎ መውጣት ፈልጌያለሁ፡፡ለምን ብትሉኝ ጓደኞቼ የሉም÷በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ደግሞ በፀጥታ ያካሉ፡፡ጥሎብኝ ጀርባውን የሚያክ ሰው ያሳቅቀኛል፡፡ ፊትለፊቴ ከተቀመጡት የሙቀት ምርኮኞች መካከል የሰማይ ስባሪ የሚያህል ወጣት፤ የቆላ ዝንብ የሚያህል (እንትን) ከጀርባው ላይ ዘግኖ በመገረም እያየው ሳለ እኛም ስላየነው ደንገጥ ብሎ፣
‹‹እኛ ሰዎች እኮ ስንባል ቆሻሾች ነን…›› ከማለቱ
‹‹እሱ ፎከት እኮ ያንተ ነው እንጂ..›› አንድ በራ ጭንቅላት ሰው መልስ ከመስጠቱ፤በሳቅ ፀጥታችን ደፈረሰ፡፡ ከትንሽ ሰጣ ገባ በኋላ ድጋሚ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ እንዲህ ያልበላውን የሚያክ ከሚመስል ሰው ይህን ያህል ‹‹እንትን›› ከጀርባው ላይ ተቆፍሮ መውጣቱ ገርሞኛል፡፡ ማከኩ መታከኩ እንደቀጠለ ነው፡፡ የሰው ልጅ ጀርባውን እንዲያ ሲያክ እንዲህ ያለ ሲጥሲጥታ ይወጣል ብዬ አልገምትም ነበር፡፡ አጠገቤ የነበረን ጥቁር ልጅ ‹‹አባቱ መስታወትሽን እንዳትጎጂው›› አለው ከመጀመሪያው ጀምሮ በቅናት ዓይን ሲከታተለው የነበረ ጠይም አዳራ መሳይ ልጅ፡፡ ጥቁሩ ልጅ በንቀት ገላመጠውና ማከኩን ቀጠለ፡፡
ዛሬ አለም አቀፍ ጀርባ የማከክ እና ማሳከክ፣ መተካከክ፣እከክ…ቀን መስሎኝ ‹‹ቀኑ ዛሬ ምንድን ነው?›› ብዬ ልጠይቅ ዳዳኝ ወዲያው ተውኩት፡፡
ከሳውና ባዝ ተወልውለህ ስትወጣ ሰዎች ሁሉ ቆሻሻ እንደሆንን የምትረዳው በአፍንጫህ ነው፡፡ እውነት ለመናገር መዓዛዋ፣ጠረኗ የሚናፍቅር ቆንጆም ሆነች ፉንጋ ወዳጅ ብትኖርህ ከሳውና ባዝ ስትወጣ አደራህን እንዳታገኛት፡፡ልትታዘባት ትችላለህ፡፡የጠረን ሻምዮንነቷን ልትቀማት ትችላለህ፡፡ ያ ጠረኗ ናፍቆህ በሰላምታ ሰበብ ጉንጯን አልያም ከንፈሯን ሳም ልታረግ ጠጋ ብትል የፎገራ ከብት÷ የፎገራ ከብት ልትሸትህ ትችላለች፡፡ደንግጠህ አፍንጫህን እየነካካህ ‹‹ገላሽን ከታጠብሽ ቆየሽ..እንዴ?!›› ልትል ይዳዳሃል፡፡
የከብትን ነገር ከብት ያነሳዋል እና ወደ ጊዜያዊው ስቱድዮ ልመልሳችሁ፡፡ አንድ የከብት ነጋዴ ነኝ ያለ ሰው ከአንድ ቀጭን ሽማግሌ አጠገብ ያን ያልተመዘነ ግዝፈቱን እንደያዘ ተቆልሎ በሽማግሎው ጥንካሬና የቆይታ ብቃት እንደተገረመ፤እጁን ከጀርባው ላይ ሳይነቅል ‹‹ፋዘር አልተቻሉም እኮ፤ጠንካራ ንዎት፤እስካሁን ሳይወጡ…›› ከማለቱ
‹‹እኔ እኮ ከናንተ የማዳበሪያ ትውልድ አይደለሁም›› በፍጥነት ከመመለሳቸው፤ሳቅ ተከተለ፣ጨዋታው ደራ፡፡ የሁለት ትውልድ ፉክቻ ተጀመረ፡፡ እየተወራ፣እየተወራ ስለኑሮ ውድነት ቀጠለ፣ስለ ትዳር ተነሳ፣ስለሴቶች ተነሳ፣ስለአስቸጋሪ ሴቶች፣ሃብታም ሴቶች፣የድሮ ሴቶች፣የዘንድሮ ሴቶች… አቤት ሴቶች የሴቶች ነገር እንዳለ ሰዓቱን ወሰዱብን እኮ…ጨዋታው ቀጠለ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ቅድም በዱሮውና በዘንድሮው ትውልድ ፉክቻ ቁጭትና ቂም ያደረበት አጠገቤ የተቀመጠ በወጣትነት ካርድ የተመዘገበ ገጣጣ ጎልማሳ የበለዙ አይኖቹን እያሸ ‹‹የዱሮ ትውልድ ከኛ በልጦ መስሎህ ነው፤ የት መሄጃ አላቸው፡፡እኔ እንደሳቸው ባረጅ ፣ጡረታ ብወጣ እንኳን ሳውና ባዝ ረጅም ደቂቃ መቀመጥ ይቅርና ምጣድ ላይ ቁጭ አልልም እንዴ!›› እያንሾከሾከ ነገረኝ፡፡ ለምን ለኔ ብቻ ይነግኛል ‹‹ ከፈለክ ጮክ ብለህ ለሁሉም አትናገርም እንዴ እኔ የሳውና ባዝ ኮሜንታተር ነኝ እንዴ?!›› ብዬ ልጮህበት ቃጣኝና ተውኩት፡፡
ዛሬ በጊዜ ብወጣስ፤የጀርባ እከክ ቀን ይመስላል እኮ፡፡ ያለ ቀኔ መጥቼ ጀርባዬን ከማደማ ብዬ ተነሳሁ፡፡ የተወለወለ ብርሌ መስዬ ስመጣ..በዓል መድረሱ ትዝ አለኝ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?

ግብረ ሰዶማዊነት፤ሌላኛው ጋሬጣ