ባልና ሚስት


ችግር ቁምነገራችን ነው፡፡ ድህነት ልብሳችን ነው፡፡ ልጅነት ደግሞ የድህነት ዘባተሎን የሰበሰበ የቁምነገር ኮሮጇችን ነው፡፡
ልጅነቴን ካደመቁልኝ ታላላቅ ችግሮች መካከል በቤት እጦት ከሰፈር ሰፈር መጦዛችን ነው፡፡ ተወልጄ ለአቅመ መዋዕለ ሕፃናት አልፎም እስከ ሦስተኛ ክፍል ዕድሜዬ ሕይወትን ያሟሸሁባት በመሆኗ እጅግ እወዳታለሁ፡፡ ውቤ በረሃ፤ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወረድ ብሎ የነ ካሳ ገላግሌ ሰፈር፡፡ ጣፋጭ ትዝታዎችን በአምቦቀቅላ አእምሮዬ ሸክፌ የወጣሁባት ሰፈር ናትና ‹‹ያን ሰፈር ግን ለምን ለቀቅን?›› እል ነበር በልጅነት የቁጭት ስሜት…‹‹ኸረ እንኳን ለቀቅን፤ቤት አልባ እንሆን አልነበር?›› እላለሁ ዛሬ በበሰለው ሕሊናዬ፡፡
ከእኩዮቼ የሰፈራችን ልጆች ተነጥዬ የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ በመሆኔም የተሻለ የትምህርት ዕድል የተፈጠረለት ሕፃን (ስኮላርሽፕ) ያገኘ ተብዬ እቆጠር ነበር፡፡ ቂቂቂበነገራችን ላይ ለዚህ ጥረታቸው ወላጆቼን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ ዛሬስ እሱ ውለታውን ይክፈላቸው እንጂ እኔማ የኮንዶም ለምኔ ..ይቅርታ የኮንዶሚኒየሜን እንኳን ለባንክ ማጉረስ አልቻልኩም፡፡
ከትዝታ ማህደሬ ውስጥ መዘዝ አድርጌ አንድ አሮጌ የትዝታ ዶሴ እንካችሁ ልበላችሁ፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን በሰፈራችን ሜዳ… (ይግረማችሁ ውቤ በረሃ ያኔ ሜዳ ነበራት..ለዛውም የኛ ሰፈር ሳይቆጠር እንጢቅ ነዋ!)...እቃ እቃ፤ባልና ሚስት ልንጫወት ተሰባስበናል፡፡ የሙሸሮች ዳስ ተዘጋጀ፡፡የጭቃ ኬክ ተሰናዳ፡፡ እንግዲህ የቀረው ማንባልማንሚስትይሁን የሚለው ነበር፡፡አይግረማችሁ፤የዛሬን አያድርገውና ከእኩዮቼ መካከል እጅግ ቀይ፣ጠጉረ ላዛ እና ሽቅርቅር የማበዛ በመሆኔ ሳይሆን አይቀርም ባልነትተመረጥሁ፡፡ አሁንም ወላጆቼን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ይኼንንም እሱ ይክፈላቸው፡፡
አይገርማችሁም የልጅነት ምርጫ? ዛሬ ቀይ የሃበሻ ወንድ በየትኛዋም የሃበሻ ሴት ዘንድ አይንህን ላፈር እንደማይባልወይ ጊዜእናላችሁ ከሴት ወገንም እንዲሁ አንዲት ቆንጂት ተመረጠች፡፡መስፈርቱ ቁንጅና ብቻ ይመስላልም፡፡ ቂቂቂ
ጋብቻው ሳይጀመር ግን ሙሽሪት ሆዴን አመመኝ እያለች ሽንት ቤት መመላለስ አበዛች፡፡አልፎ አልፎም የሆነ ነገር መጣብኝ እያለች በመሯሯጧ ከሚስትነት ተሻረች፡፡ሁለተኛዋ ሚስቴን ሲመርጡልኝ ግን የኔ ምርጫ አልነበረችም፡፡ መረጡልኝ ፡፡ምርጫውም ፍትሃዊና እኔን ያላሳተፈ በመሆኑ ቅሬታዬ አቀረብሁ፤የሰማኝ ግን አልነበረም፡፡ እንደውም ‹‹አልጫወትም!›› ስል ‹‹ለምን?›› ‹‹ጥቁር ናታ!..ታስጠላለች›› ወይ ልጅነት ሁሉም ነገር ፊት ለፊት ነው! ‹‹በቃ እምቢ ካልክ እናስወጣሃለን!›› ‹‹እምቢ!›› ደግሞ ለኩራት ማን ብሎኝ፡፡ ብዙ ተለመንኩ ‹‹ተው አግባት!?››..የጨዋታው አለቃ ትልቁ የሰፈራችን ልጅ ተናዶ፤ ‹‹ቡጣ በቃና ..ባል ሁን!›› በዚህ ዘመን እንዲህ ተጠርታችሁ ባል ሁኑ? ስትባሉ አስቡት፡፡ቂቂቂ
ቡጣ የሰፈራችን ምርጥ ጥቁር ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሳስበው መልኩ ዝም ብሎ ናይጄሪያዊ ይመስለኛል፡፡ ሕጋዊ ስሙ ናትናኤል እንደነበረ ግን ትዝ ይለኛል፡፡ ንፍጡን ወደአፍንጫው ውስጥ መልሶ እየሳበ ሲመጣ ብርሃን አልባ ፍሬቻ ይመስላል፡፡ ቡጣና ጥቁሯ ልጅ ተጋቡ፡፡ በጊዜው የምናውቀው የሰርግ ሥርዓት ሁሉ ተፈጸመ፡፡ከአይነኬው ተግባር ውጭ ማለቴ ነው፡፡ በአፋችን ጲጵ..ጲጵ እየተንጫጫን በእንጨት መኪና አጀብናቸው፡፡
ከአስርት አመታት በኋላ በአጋጣሚ በዚያች መንደር ሳልፍ፤ከማውቀው ነገር ይልቅ የማላውቀው ነገር ይበዛ ነበር፡፡አንዳንድ ነገሮች የድሮን አሻራ ሳይለቁ ቢኖሩም፤በቃ ምንም የማውቀው ነገር አለመኖሩ ባይተዋርነት እየተሰማኝ ርቄ ሄድሁ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?