የአዞ ፍቅር vs የአዞ እንባ

አርባ ምንጭን የረገጠ የትኛውም ጠጉረ ልውጥ ነጭ ሳርንና አዞ እርባታውን ሳያይ እንደማይመለስ አልጠራጠርም፡፡ እኔም እንደማንኛውም ጎብኝ እግሬ ከሄደባቸው ቦታዎች እነዚህ የመጀመርያዎቹ ናቸው ፡፡
እንደው እናንተዬ አርባ ምንጭን በሾርኔ ስሸረምማት ፅዳቷ ሸገርን አፏን ታስይዛት የለ እንዴ? እርግጠኛ ነኝ አዲስ አበባና አርባ ምንጭ በምዕናብ ቢገናኙ፤ አዲስ አበባ ገና እንዳየቻትድሮ ሳውቃት ልጅ ነበረችእያለች ካሰላሰለች በኋላ ‹‹እንዴት አባትሽ አምሮብሻል ባክሽ?!›› ብላ መደነቋ አይቀርም፤ አርባ ምንጭም ድንግጥ ብላ ‹‹እንዴ ? ምነው እንደዚህ ቦርኮ መሰልሽ አንቺስ?!›› ብላ መጠየቋ አይቀሬ ነው፡፡
አርባ ምንጭ አዞ እርባታን እንማንኛውም ጎብኜ፤ ጎብኘት፣ ጎብኘት አድርጌ ብወጣም ውስጡ ምን እንደሚመስል እዚህ ላይ ብተርክላችሁ ጊዜ እና ወሬያችሁን ማባከን ነው የሚሆንብኝ፣ ደግሞም የድሮ ጋዜጠኛ የሆንኩ ስለሚመስለኝም እርግፍ አድርጌ ተውኩት ነገር ግን አንድ ልተወው የማልችለው ክስተት ግን ከፍልቅልቅና ተጫዋችዋ አስጎብኚዬ ሰማሁ፡፡
 
ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡ በእርባታ ቦታው ውስጥ ለጎብኚዎች እይታ ከተቀመጡ አዞዎች መካከል ይህ  አዞ 26 ዓመት ጎረምሳ ሲሆን ከኋላ ደግሞ 23 ዓመት ኮረዳ አዞ ትገኛለች፡፡ እነዚህ አዞዎች በፍቅር ለረጅም ዘመናት አብረው ኖረዋል፤ ብዙ እንቁላሎችንም በአዞ አምሳል ለመፈልፈል በቅተዋል፡፡ በመሃላቸውም አንዳች ፀብ ሳይፈጠር፣አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር አብረው በልተው፣ ውሃቸውን ጠጥተው በፍቅር ለዘመናት የትኛውም አዞ ጣልቃ ሳይገባባቸው ኖረዋል፡፡(ለብቻቸው የታጠረ ቦታ ቢኖሩም ማለት ነው፡፡)
ሆኖም ከእለታት በአንድ ቀን አስተዳደሩና የእርባታው ሃላፊዎች ሴት አዞዋን በራሳቸውና ግልጽ ባልሆነልኝ ምክንያት አዛወሯት፤መቼም አዞ እንደሆነ አዞ ነው፤ ይባል የለ፡፡ የአዞ የአውሬነት ባህሪ ከእንሰሳቶች ንጉስ አንበሳም የባሰ ነው፤ምህረት የለሽነቱ ጠግቦም ቢሆን ከማደን አለማለፉ ነው፤ አዞ 150 ዓመታትን መኖር የሚችል ፍጡር፣ ራስ ወዳድ ነገር ግን ከዝርያው ጋር እጅግ ተቻችሎ የሚኖርም ነው፡፡
እናላችሁ እነዚህ ባለትዳር አዞዎች እንዲለያዩ ከተደረጉ በኃላ ወንዱ አዞ ምግብ አልበላም ማለት ጀመረ፤ ራስ ወዳድና በአንድ ጊዜ 15 ኪሎ ግራም በልቶ ሳምንት የሚተኛው ፍጡር ምግብ አሻፈረኝ አለ፤ አዞ በፍፁም ድምፅ ያለምክንያት አያወጣም፡፡ ይህ አዞ ግን ከፍቶታልና አልፎ አልፎ ማጉረምረም መጀመሩ የእንሳሰት ባለሙያዎቹን ግራ አጋባቸው፣ ጤንነቱ ቢመረመርም ምንም ችግር አልነበረበትም፤ ውሃ ሳይዋኝ የማይውለው አዞ፤ ውሃ ንክች አላረግም አለ፡፡ ነገሩን በጥሞና የተወያዩበት ባለሙያዎች አንድ መላ ዘየዱ፤ይህን መላ ሲያስቡት ሳይንስ ስለ አዞ ከነገራቸው ሃቅ የራቀ እንደሆነ ያውቁታል ግን በቃ፤ ወሰኑ፡፡ ‹‹ያቺን አዞ ስለሄደች አዝኖ ቢሆንስ፤መልሰን እናመጣትና እስኪ ሁኔታውን እንየው›› አሉ፡፡
ሴት አዞም ከሄደችበት ቦታ እንድትመጣ አደረጉ፡፡ ሁለቱም ፍቅረኞችም እንበላቸው ባለትዳር አዞዎች ተገናኙ፡፡ አስደናቂው ክስተትከዚህ በኋላ ነው፡፡ ፈጽሙ ከተኛበት የማይናሳው አኩራፊው አዞ ምግብ ለመጀመርያ ጊዜ ከወራት በኋላ ቀመሰ፣ ከእሷም ጋር አብረው ውሃ ዋኙ፣ፀሀይም ሞቁ፣ፍቅር ሰርተውም ለእንቁላል በቁ ፡፡ የእንሰሳት ባለሙዎቹን ባስገረም መልኩ አዞው አፍቃሪ መሆኑን በተግባር አሳያቸው፡፡ ስትል አስጎብኚያችን ነገረችን፤
ድንገትም አንዱ ጎብኚ ወደሌላኛው ወዳጁ ዞር ብሎ
‹‹አየህ አዞ እንኳን ያፈቅራል፤ አለ እንጂ ይሄ›› ተሳለቀበት
የኔ ባልደረባም ‹‹ወንድ ልጅ አዞ እንኳን ሆኖ ያፈቅራል›› ሲል ተሳሳቅን ፡፡ምን ለማለት እንደፈለገ ስለገባንም
ድሮ ድሮ ለምን ‹‹የአዞ እንባ›› እንደሚባል አይገባኝም ነበር፡፡ ዛሬ ሳየው እንዴትም የማያለቅስ ፍጡር እንደሆነ ከሁኔታው የገባኝ መሰለኝ፡፡ እርግጥ አዞ አዝኖም ሆነ ታሞ፣አልያም አደጋ ገጥሞት እንባ የሌለው ፍጡር፣ ከአስፈሪ ገፅታው ባለፈም የበላው እንዲዋሃድለት ቀኑን ሙሉ ውሃ ውስጥ፣ጥላ ላይና ፀሃይ ላይ እያፈራረቀ አፉን ከፍቶ የሚተኛ ፍጡር ነው፤ ነገር ግን እንባ ያላሸነፈው ፍቅር ያሸንፈዋል ብሎ የሚገምት ማን አለ? እንዲህ ግርማው የሚያስፈራ፣ አእምሮ አልባ ፍጡር ድንገት ላላወቀው ስሜት እጁን ይሰጣል ብሎ ማንስ ይገምታል?! ስንቱን ፍጡር ሲያድን ቅንጣት የማይራራው አውሬ ‹‹ፍቅር›› ለሚሉት ግሳንግስ ስሜት እጅ ይሰጣል ብሎ ማን ጠበቀ ?ማንም!

Comments

Popular posts from this blog

ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?

ብቸኝነትና ግለኝነት የዘመኑ ወረርሽኝና ሰለባዎቹስ እነማን ናቸው?

ራሰ በራበት እንዴት ሊቀር ይችላል? የራሰ በራነት መድሐኒቶችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?