….‹‹ክረምቱን በ‹ናዝሬት›…››……
ዘመን
መፅሔት(ያልታተመ)
እንደ ኑሮ ውሽንፍር የሚጋረፈውን
የአቃቂ ብርድ የቀመስኩት ገና ከመኪና ከመውረዴ ነበር፡፡ ግን እኔ ብቻ ሳልሆን ያካባቢው ሰውም ውርጭ እንደጨመደደው ከፊቱ ስለሚታይ
ተፅናናሁ፡፡ እኔና ባልደረቦቼ እንደምንም ብለን መናኸርያው ልንገባ ስንል የተለመደው የመናኸርያው ወጣቶች ወከባ ተቀበለን ።ለነገሩ
ካዲስአባባ የምንሸሽ እንጂ ለስራ የምንሄድ አንመስልምም
‹‹ዝዋይ ናቹ አይደል!...ኑ!››
ጉተታው ተጀመረ
‹‹ልቀቃቸው ደብረዘይት
ናቸው›› ሌላኛው ተናነቀው ይሕኛው ደግሞ እሚጠነቁል ይመስላል።
……‹‹ አቦ
ዞር በሉ ሞጆ ናቸው›› ሌላኛው ሁለቱንም ገፈተረ
‹‹አይ አሜሪካ ነኝ!››
በመልሷ ብሽቅ ያለው ወጣት ደግሞ ‹‹ በሕልምሽ እንኳን አትሔጅም!!!›› ሲላት
እርሷም እኛም ሳቅ በሳቅ ሆንን፣
በመሃል አንድ አቅሙን
ያወቀ ቀጫጫ ወጣት ያልታጠቡ አይኖቹን በጣቶቹ እየጨቆናቸው፣ ወደኔ
ቀረበና ድምፁን ዝቅ አድርጎ
‹‹ አዳማ ናችሁ አይደል?!›› ሲል ወደኃላ በሸሸው ጥርሱ ትክክለኛ አማርኛ
ለማውራት ሞከረ፤ እንደኔ ግምት ግን አንዳንድ ቃላት በጥርሱ መሃከል ያመለጡት ስለመሰለኝ እንዲደግምልኝም ፈለግኩ ደግሞ እኮ በዚህ ስራ ምን ያህል ዘመን እንደሰራ የሚያሳብቅበት ይመስላል፡፡
ብዙ ጊዜ ፀጉር ሲሸሽ እንጂ ጥርስ እንዲህ ወደ ኋላ ሲሸሽ ባለማየቴ ለመሳቅ ቃጣኝ…ግን በዝምታ መከተሉን መረጥኩ...
በኌላም አንዱ መኪናው
ውስጥ ወስዶ ዶለን፡፡ ገና ከመግባታችን ደግሞ ሹፌሩ በቅርቡ ታርጋው ተፈቶበት ነበርና የመንገድ ትራንስፖርት ሃላፊዋን በሌለችበት
ከረዳቱ ጋ በመተባበር መሳደብ ጀምሯል፣
‹‹ቆይ እቺ ቋሚ ድሃ፤
መንገድ ላይ ላግኛት እንደ ዝንብ ነው የምጨፈልቃት!››….ተሳፋሪ ሁሉ በሳቅ አውካካ
‹‹ወይ አላሰሩን ወይ
አላስተማሩን፤ 10ኛ ክፍል በፀሎት ጨርሳ ኪሳችንን ስለት ማስገቢያ ታደርገዋለች….ወይኔ!…›› ረዳቱ አጉተመተመ አሁንም እየሳቅን
ነበር፣እንዲህ እየተዝናናን አልፎ አልፎም እንደነገሩ እያንቀላፋን ደረስን፡፡
ብዙ ጊዜ አዳማን በክረምት
ብመርጣትም ዕድሌ ሆኖ በንዳዱ ሰዓት ካልሆነ በክረምትየመቆየት እድሉን አላገኝሁም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን የተሳካ ይመስላል፡፡
በጋ ይሁን ክረምት--ለተመልካች
በማይገባ መልኩ እጅግ ለስላሳ አየር በስሱ ይነፍሳል፤ መጠነኛ ሙቀትም ስላለ በቲሸርት ለመንቀሳቀስ እንደሚመች ባብዛኛው ነዋሪ አለባበስ
ላይ ይታያል፡፡
ዛሬ ዛሬ አዳማን ከሌሎች
ከተማ የሚለያት ነገር ቢኖር የዘመናዊ ሆቴሎች መብዛትጋር ተያይዞ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መምጣቷ ነው፡፡ እጅግ ላስተዋላት
ሰው ገጿጭቃ ውስጥ እንደሚጫወት ህጻን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቆሸሸ የመጣችው
አዲስ አበባ ለሃገር ውስጥም ሆነ ለአለም አቀፍ ስብሰባዎች መቀመጫነት አልመች ብላ የምትጎረብጥ በርጩማ ስላስመሰላትም ይመስላል
አብዛኞቹ የኣዳማ ሆቴሎች በኮንፈረንስና በስብሰባ የሚጨናነቁት፤ በተለይ ከረምት ተመራጭ የሚያደርጋትም የአየር ንብረቷ ነው፡፡
……..የማያርፈው እግሬ አሁንም ይዞራል፡፡ ዓለም ማጀላንና ኮሎምቦን
አልያም ቢጤ አሳሾን ያወድሳል፤ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግን ጋዜጠኞች ያልረገጡት፣ያልገቡበት ቦታ የለምና ይህ ክብር ሊሰጠን
ይገባል ብዬ ብከራከርም የሚሰማኝ ግን አአላገኘሁም፡፡ ያም ሆነ ይህ መጓዜን አላቆምኩም፡፡
አመሻሹን ጠብቄ ካረፍኩበት ሆቴል ተነስቼ እግሬ ወዳመራኝ አንድ መንደር ዘው አልኩ፡፡ እንደው ስሟ ባይታወቅም ከመብራት ሃይል ሰፈር በተቃራኒ አቅጣጫ
ያመራ ከዚች ሰፈር ጋር ይላተማል፡፡ይች መንደር የባህዳሯን ‹ኮሽኮሽ› ፣የሸገሯን ‹ጨርቆስ› ሰፈር አስታወሰኝ… እናም ምሽቱን ተከትሎ
እንግዶች ይመጡ በጉጉት የሚጠብቁ መደዳውን የተኮለኮሉ ትንንሽ ካቲካላ ቤቶች አሮጌ የሳንቃ በሮቻቸው ከፊታቸው እንደደንቃራ ለተገተሩ
ሴተኛ አዳሪዎቻቸው ቦታውን ለቀዋል፡፡ ፊት ለፊታቸው እጅግ ዘመናዊ ባሮች ተገትረዋል፡፡ ታሪካዊ ፍጥጫም ይመስል መሳ ለመሳ እየተያዩ
ደንበኞች ይነጣጠቃሉ፣ ፣ይገለማመጣሉ፣ አልፎ ግልፅ ጦርነት ያካሂዳሉ በብዛት ግን ድምፅ አልባው ጦርነት ነጎሷል….
ይችን መንደር አልፌ ከመሄድ በፊት አንድ ጥያቄ ውስጤ አጫረብኝ… አንዱ
ባር ዘው አልኩና ጥያቄዬ እስኪመለስልኝ ድረስ በትዕግስት ተስተናገድኩ
ውር ውር የሚል አንድ አስተናጋጅ ጠራሁና ለመግባባት ሞከርኩ፣ ጥሎብኝ
ደግሞ ከሰው ጋር ቶሎ መግባባትም ሆነ ማግባባት አይሆንልኝም እስክላመድ ድረስ እንጂ…
‹‹ ለምንድን ነው ጭፈራ ቤቶቹ ሁሉ የሰው ድርቅ የመታቸው?›› ወደ
ገደለው ጥያቄዬ አመራሁ…
‹‹ምን ባክህ ፆም ሲገባ ሁሌም እንዲህ ነው፤በረመዳንም፣ በሁዳዴም
ሰው የለም››
ደሞ ተነሳሁ መጓዜን ቀጠልኩ ፤አዳማ እንደ ሸገር በምሽት ለመንቀሳቀስ
የምታሰጋ ከተማ ባለመሆኗ የማሰስ ጥማቴን ከሌላው ጊዜ ያረካሁ እስኪመስለኝ ወጣሁ፣ወረድኩ…ታጠፍኩ፣ተጠመዘዝኩ፣ አመራሁ፣አቀናሁ….
በመጨረሻም በሙገር ሰፈር ሽቅብ ወጥቼ በፖስታ ቤት ጫፍ ብቅ እንዳልኩ
የአዳማው ፒያሳ ‹‹ፍራንኮ ሰፈር›› አልመሸም ገና ነው የሚል ይመስል በመብራትና ሙዚቃ ድለቃ ደምቋል፡፡ አሁንም እግሬ ወዳመራኝ
አንድ ካፌ ዘው አልኩ፣ ኦልያድ ሲኒማ ስር፡፡ ኦልያድ ሕንፃ ላይ ቁጭ ያለ ማንም ሰው አዳማን በሾርኔ አቅጣጫም ቢሆን መገርመም
ይችላል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የአዲስ አበባ ተራራማ ቦታዎችን ሰንጥቆ የሚመጣው አውሎ ንፋስ የደብረዘይት ውሃማ አካላት የሚያስነሱት
የንፋስ ሃይል ጋር በማበር አዳማን ዝቅ ብሎ ሲያሸብራት ነበከተማዋ ከፍታ ቦታዎች ያለእረፍት በሚሽከረከሩት የንፈስ ሃይል ተርባይኖች
ይረዳል፡፡ እንደውም አዳማ የታደለችው የንፋስ ሃይል ነው ማለት ይቻላል፡፡
ይህን ሃይል ወደ ተግባራዊ ሃይል (processed energy) መቀየር መቻል ብዙ ጥቅም እንዳለው አሁን ገና የተነቃ ቢሆንም….
‹‹ እግዜር ሳይደግስ አይጣልም›› እንዲሉ ይች ከተማ ሃይለኛ ንፋስ
ባይኖራት ኑሮ ቀደምት ነዋሪቿ እንደማይሰፍሩባትና ቢሰፍሩም እንኳ ሙቀቷ ወደ ተራራው ሳያሰድዳቸው እንደማየቀር አልተጠራጥርኩም።
የምሽቱን ድባብ ማጣጣሜን ቀጠልኩ… ናዝሬት ሃይለኛ ንፋስ ሲመጣም ያካባቢው ሰው አስቀድሞ ከተገነዘበ ሁሉም ወደ ቤቱ ለመግባት ይጣደፋል፣ይሯሯጣል
አለበለዚያ ንፋሱ ያለ የሌለውን አቧራና ጠጠር ያለምንም ማስጠንቀቂያ በቆሙበት ያለብስዎታል፡፡ እንግዳ ከሆኑ ደግሞ ማማለጥ አይችሉበትምና
አሜን ብለው መቀበል ነው፣ማን ከተፈጥሮ ጋር ይከራከራል!..
እግረ መንገዴን አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ የነገረኝን ቀልድ ደግሞ ላካፍላችሁ….
ናዝሬትየሚለው የከተማዋ ስያሜ በ አዳማ ሲቀየር አንድ የሃይማኖት አባት (ከየትኛው ሃይማኖት እንደሆነ እርግጠኛ ባልሆንም)
ስብከቱን ቀየረና
‹‹የኣዳማው እየሱስ ያውቃል›› ሲል ሰበከ አሉ፡፡
አሁንምቁጭ ብዬ ስለዚች
ከተማ ማሰቤ አልቀረም…. እስኪ ስለ ናዝሬት የተዘፈነ ዘፈን ካለ ብዬ ሳስብ አልመጣልህ አለኝ… ግን ኋላ ላይ አንድ ዘፈን ብቅ
አለልኝ….
ክረምቱን በናዝሬት ባዳማ
ከተማ
ምሽት ለግር ጉዞ የምትወጣው
ቀድማ…….
መቼም ይህን ዘፈን ታውቁታላችሁና
ብዬ ተውኩት፤ ክረምቱን ባዳማ በእርግጥም ማንኛችሁም እንደምትመርጡት
አልጠራጠርም፡፡ እኔ ግን አበቃሁ …እስከዛሬ ያላስተዋልኳቸው ገና ብዙ ነገሮች እንዳሉ ከወዲሁ ትከሻዬ ነግሮኛልና… ልሰናበታችሁ
Comments
Post a Comment