ግብረ ሰዶማዊነት፤ሌላኛው ጋሬጣ
በዘመነ ዩሐንስ
ዘመን መፅሔት/2005 ዓ.ም
ዘመን መፅሔት/2005 ዓ.ም
አንዳንድ ጊዜ ባህላችን እና አመለካከታችን በውስጣችን የተፈጥረ ባዕድ ችግር እንዳንፈትሽ ፤
አይነኬ ያልናቸውን ገበናዎቻችን በጉያችን እንደሸሸግን ላናነሳቸው፤ ውግዝ ያልናቸውና ውስጥ ውስጡን ስር እየሰደዱ የመጡ መጤ ችግሮቻችንን
አፍረጥርጠን ላናወራባቸው የሕሊና በራችንን እንደከረቸምን የኋላ ኋላ የማንቋቋመው ሲሆንብን ‹ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ› አይነት
መፍትሄ ፍለጋ ከረፈደ እንሮጣለን፡፡
ሚስጢራዊ ሕይወታቸው በመሃከላችን መኖራቸውን እንኳን እንዳናስተውል አድርጎናል፡፡ እርስ በእርሳችን
በጥርጣሬ ከመተያየት ባለፈ ምንም ማድረግ የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡ዛሬ ላይ ብልጭ ድርግም በምትል የመገናኛ ብዙሃን
ማሳሰቢያ አልፎ አልፎም ቢሆን ሲነገር እንሰማለን፡፡ ሆኖም ጉዳዩ አሳስቦት ወደ መፍትሔ የመጣ፣ ይመለከታኛል የሚል ግለሰብም ሆነ
የመንግስት አካል የለም፡፡ ችግሩ ግን አለ ብቻም ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ተከታዮቹ እየጨመሩና አያሌ ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ድብቅ
ማህበረሰብ እየተቀላቀሉ አስፈሪ አደጋ ከፊታችን እንደተጋረጠ ምልክት ሆነውናል፡፡
ራሳቸውን «ዜጋ» እያሉ ይጠራሉ፡፡ ብዙዎቻችን ባለማወቅ የነሱን አለባበስ በመልመዳችን በመሃከላችን
መኖራቸውን እንኳን ማወቅ ተስኖናል፡፡ ዝምታችንም ውስጥ ውስጡን እንዲባዙና አዳዲስ መሰል የነሱ አይነት «ዜጋ» እንዲያፈሩ መንገድ
ፈጥሮላቸዋል፡፡ ግብረሰዶማውያን በመዲናችን ብቻ ሳይሆን እንደ ሃዋሳ ባሉ ታዳጊ ከተሞች እየበዙና እየተጠናከሩ መምጣታቸው ባህላችን፣ማንነታችና
እምነቶቻችንን ሊነቀንቁት እየተሰናዱ ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል አንዳንድ የሕትመት ውጤቶች ቁጥራቸው 16,000 መሆናቸውን አሁን ላይ
ደግሞ አዳዲስ ጥናቶችና ጽሑፎች ወደ 30,000 ገደማ እንደሚደርሱ አመላክተዋል፡፡
የምዕራባውያን የባህል ወረራ ያልፈተነው ሃገርና ህዝብ የለም እስኪባል ድረስ ጠቃሚውም ጎጂውም
ባህላቸው በብዙዎቹ የዓለማችን ሃገራት ላይ ተጽዕኖው በየጊዜው ማረፉም አልቀረም፡፡ የዘመነ ገሎባላይዜሽን ትሩፋት ከሆኑ ጎጂ ባህሎች
አንዱ እንደሆነ አያሌ ጸሐፍቶች ቢተቹም ምዕራባውያን ግን ሥራዬ ብለው ከማስፋፋት ወደኋላ አላሉም፡፡
የታሪክ መዛግብቶች ግብረሰዶማዊነት ከክርስቶስ ልደት በፊት በጥንታዊ ስልጣኔዎች ወቅት የተጀመረ
እንደነበረ እና የመጀመሪያዎቹ ግብረሰዶማውያን ተብለው በታሪክ መጽሐፍት
የተመዘገቡት ክኑምሆቴፕ እና ኒያንኩኑም የተባሉ ሁለት ግብፃውያን ወንዶች ከክርስቶስ ልደት 2400 ዓመተ አለም እንደነበረ ይታወቃል፡፡
በጥንታዊት ግብፅ፣ ፐርሺያ፣ ግሪክና ሮም ውስጥ በስፋት የተገኙ የታሪክ መረጃዎች ይህ ተግባር እንዴት ይፈጸም እንደነበረ ያሳዩናል፡፡
በአንዳንድ የታሪክ ወቅትም በዚህ ተግባር የሚጠቀሱ ነገስታቶችና የጦር አበጋዞች እንደነበሩም ይታወሳል፡፡በታላላቅ የሃይማኖት መፅሃፍትም
ላይ ግብረ ሰዶማዊነት እንዴት እንደመጣ የተቀመጡ መረጃዎችም እናገኛለን፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን የአለማችንን ሁኔታ ስንፈትሽ ደግሞ ይህ ከተፈጥሮ ህግጋት ውጭ የሆነ ጾታዊ
ግንኙነት ያልበረዘው ሃገር፣ህዝብና ባህል የለም ማለት ይከብዳል፡፡ የችግሩ መስፋፊያ የሆኑት ምዕራባውያን እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን
አጋማሽ ድረስ በተለያየ መልኩ ሲከላከሉት ቢቆዩም ዛሬ ላይ ግን አብዛኞቹ ህጋዊ እስከማድረግ ደረጃ ደርሰዋል፡፡
እስከ 1970ዎቹ መጨረሻም በመላው አውሮፓና አሜሪካ የአዕምሮ ችግር ተደርጎ ህክምና ሲሰጥ
ቢቆይም ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶችን ከጎናቸው በማሰለፍ ይህ እንዲቀር ጥረታቸው ሰምሮ ዛሬ ላይ ላሉበት ከተፈጥሮና ሃይማኖታዊ
ሃቆች ውጭ የሆነውን ስርዓት እስከመቀበል የደረሱ ሀገራት በዝተዋል፡፡
ቀደም ሲልም በስነልቦናው ትምህርት sexual deviation በግርድፉ ወደ አማርኛ ስንመልሰውም
ያፈነገጠ የወሲብ ባህሪ በመባል ይገለጽ ነበር፡፡ ነገር ግን ቁልፍ የመንግስት ቦታ ላይ የነበሩና ተሰሚነት የነበራቸው አንዳንድ
ሰዎችም ሕይወታቸውን በዚህ መልኩ ይመሩ ነበርና በተለያዩ ጥረቶችና ሚዲያው ላይ ባካሄዱት ሰፊ ቅስቀሳ በ1974 ዓም ከአዕምሮ ህመም
መዝገብ ላይ እንዲፋቅ ማድረግ ችለዋልም፡፡
ኢትዮጵያውያን በግብረሰዶማዊነት ሕይወት
በቅርብ ጊዜያት በግብረሰዶማውያን ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ግለሰብ በማግኘትም ስለ ጉዳዩ ሰፊ መረጃ
ወሰድን፡፡ ስለችግሩ አሳሳቢነት በአግባቡ የሚያነሳ፤ ትልቅ ግንዛቤ
የሚሰጥ በመሆኑ የሃሳባችን ማጣቀሻ አደረግነው፡፡ አቶ እሱባለው ታደሰ ይባላሉ፡፡ የጤናና ስነልቦና ባለሙያ በመሆን ለ16 አመታት
ሰርተዋል፡፡ በአሁን ሰዓት በጉለሌ ክ/ከተማ የኤች አይቪ ኤድስ አስተባባሪ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የሰሩት ጥናት እና በአይነቱ የመጀመሪያ ስለሆነም በቅርቡ ለህትመት ይበቃል፡፡ ስለጥናታቸውና በጥናታቸው ስላካተቷቸው ግብረሰዶማውያን ሁኔታም አጫወቱን፡፡
ግብረሰዶማውያን በድብቅ በሚንቀሳቀሱባት ኢትዮጵያ ማህበራዊ ሒይወታቸውንም ሆነ ድብቁ የወሲብ
ቅሌታቸውን እጅግ ጥብቅ በሆነ ሚስጢር ያከናውናሉ፡፡ «እነዚህ ኢትዮጵያውያን በሁለት ወንዶች መካከል ወይም በሁለት ሴቶች መካከል
በሚፈፀም ወሲብ ብቻ አይወሰኑም ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚፈጸም የቡድን ወሲብ (communal sex) ጭምርም እንጂ፡፡ በዚህ
ብቻም አያበቁም፡፡ በግንኙነታቸው ሒደትም አንደኛው ከሌላኛው መስረቅ የተለመደ ነው፡፡ የፍቅር ግንኙነቶቻቸውም ለረጅም ጊዜ የማይቆይ
ነው፡፡» ሲሉ አቶ እሱባለው ጥናታቸው ያገኘውን ውጤት ይገልፃሉ፡፡
በከተማችን አዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ታዳጊ ከተሞች በድብቅ ከሚያከናውኗቸው ድርጊቶች መካከል
ሰርግ ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ አቶ እሱባለው በጥናታቸው ውስጥ ያካተቱትና እንደ ምሳሌም «አንድ ግለሰብ ስምንት ጊዜ ጋብቻ ፈጽሟል»
ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡ ጋብቻቸውም እጅግ ጥብቅ በሆነ ምስጢር ተጠብቆ የሚቆይና በመጨረሻው ሰዓታት ብቻ በመሃከላቸው የሚነገር ነው፡፡
የሠርጋቸው ወጪና ዝግጅትም ባህር ማዶ ባሉ ዲስፖራውያን ሙሉ በሙሉ የሚሸፈን ሲሆን ጋብቻው ቢበዛ ከ4 እስከ 6 ወር በላይ አይቆይም፡፡
በዚህ ሂደትም አንድ ወንድ ወይም ሴት ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ከአንድ በላይ ጋብቻ ይፈፅማሉ፡፡
«ስለማናውቀውና ስለማንሰማው እንጂ ብዙ ጊዜ በየ6 ወሩ በድብቅ የሚፈጸመው ጋብቻ ግብረሰዶማዊ
በሆነ ግለሰብ ቤት ውስጥ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሆቴሎችም ሰርጉ እንዲፈጸም ይፈቅዳሉ፡፡» ይላሉ አቶ እሱባለው፡፡በዚህ የሰርግ
ስነስርዓታቸው ውስጥም ሁሉም ነገር ይደረጋል፡፡ባል፣ሚስት፣ሚዜዎች ይኖራሉ፡፡ቀለበት፣ፊርማና የጥሪ ካርድ የመሳሰሉ ነገሮች ሁሉ ይዘጋጃሉ፡፡ ‹‹ሌላው አስገራሚ ክስተት በቬሎና በካባ ጋብቻ መፈፀማቸው ነው››
ይላሉ አቶ እሱባለው፡፡ በሰርጉ ስነስርዓት መሰረትም የወንድ ግብረሰዶማውያን ሚዜ የሚሆኑ ሴት ግብረሰዶማውያን ናቸው፡፡ከቤ የሆነች
ግብረሰዶማዊ ለባል ግብርሰዶማዊ ሚዜ ስትሆን ለታ የሆነች ግብረሰዶማዊ ሚስት ለሚሆነው ግለሰብ ሚዜ ትሆናለች፡፡
እንደ ጥናቱ አገላለጽም አንድ
ግብረሰዶማዊ በአጠቃላይ እድሜው በአማካኝ ከ500 ሰዎች በላይ ወሲብ ይፈጽማል ማለት ነው፡፡ በሰባት አመቴ ተደፍሬ ወደዚህ ሕይወት
ገባሁ ያለ ሌላ ግብረሰዶማዊ ደግሞ እስካሁን ማለትም እስከ 32 ዓመቱ ድረስ ከብዙ ሰዎች ጋር ወሲብ ፈፅሟል፡፡ ይህን ሕይወት ወደውም
ተገደውም የገቡበት ወገኖቻችን ተመልሰው የራሳችን ጠላት ሲሆኑ ዝምታን መምረጥ ተገቢ ባይሆንም ጊዜው ግን አልረፈደምና ከምንጩ ማድረቁ
የተሻለ መፍትሔ ነው፡፡
የችግሩ ሥር
እንደእርሳቸው አገላለጽም ግብረሰዶማውያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙና እየተጠናከሩ መጥተዋል፡፡
ውስጥ ለውስጥ በመሃከላቸው የሰሩትም መረብ መበጠስ የሚቅተን ወቅት ሊመጣ እንደሚችል የጥናታቸው ድምዳሜ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የአቶ
እሱባለው ጥናትም ሆነ አንዳንድ የሕትመት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት የችግሩ መንስኤ ግብረሰዶማዊነት እንዲስፋፋ ያስቻሉ ሁኔታዎች በሃገራችን
መፈጠራቸው ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ግብረሰዶማዊነት ወደ ሃገራችን እንዴት እንደገባ ባይታወቅም እንዲስፋፋ አስተዋዕጾ
ያደረጉ ምክንያቶች ግን ይታወቃሉ፡፡ አቶ እሱባለው እንደሚሉትም ዲያስፖራ ኢትዮጵያውኖች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ
ያሉ ዲያስፖራውያን በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲለመድና ተቀባይነት እንዲኖረው ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በሁለተኛነት
(በስኮላርሺኘ) የውጭ ትምህርት ዕድል ሰበብ ኢትዮጵያውያንን ወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በመውሰድ ይህን ተግባር እንዲማሩ በማግባባትና
እንዲለምዱት ካደረጉ በኋላ ወደ ሃገር ቤት በመላክ የራሳቸውን ዜጎች እንዲበክሉ ከፍተኛ ጥረቶች ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡ ብዙውን
ጊዜም ይህ ሲሰምርላቸው ይታያል፡፡
በከተሞቻችን በተለይ ችግሩ በግልጽ እንዳለባቸው የሚጠቀሱት አዲስ አበባና ሃዋሳ ላይ ለመስፋፋቱ
ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ከተሞች ውስጥ በስፋት አሳሳቢ እየሆነ የመጣው ወንድ ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለው የወሲብ ጥቃትና
መደፈር እንደዋነኛ መንስዔነት ይገለጻል፡፡ ለሴት ግብረሰዶማውያን መብዛት እንደ ምክንያት የሚታየው በሃብትና ንብረት በመታለል ወደዚህ
ሕይወት የሚገቡበት አጋጣሚዎች መኖራቸው ሲሆን በልጅነታቸው ወሲብን ከተመሳሳይ ጾታ ጋር እንዲፈጽሙ የሚያደርጋቸው እጅግ የተወሳሰበ
የስነልቦና ቀውስን የሚያስከትል ጾታዊ መቀራረብና መላመድን ያዳብራሉ፤በሂደትም ከተቃራኒ ጾታ ይልቅ ለተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ፍላጎት
ይጨምራል፡፡ ይህ ባህሪም ዳብሮ ግብረሰዶማዊነት ይመርጣሉ፡፡
ሴት ግብረሰዶማውያን ወሲብን በተለያየ መልኩ የሚፈጽሙ ቢሆንም ለዚሁ ተብሎ በምዕራባውያን ኩባንያዎች
የሚመረቱ የወሲብ መሳሪያዎች (Hardcore, soft core) ተብለው በሚታወቁ መሳሪያዎች አማካኝነት ነው፡፡ በጥናቱ ላይ ስሟ
ያልተጠቀሰ አንዲት እንስት ወደዚህ ሕይወት እንዴት እንደገባች ስታስታውስም ‹‹በአንድ ወቅት በተዋወቅኳት ቱሪስት አማካኝነት ነበር፡፡
የምታደርገው ነገር ሁሉ ስለምታዝንልኝና ስለምትወደኝ ይመስለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ ወደዚህ ሕይወት እንድገባ ምክንያት
የሆነ መቀራረብ ፈጠርን፡፡ ከእርሷ ጋር ሆኜ ምንም የሚቸግረኝ ነገር ባለመኖሩ ተስማምቼበትና አምኜበት የወሲብ ጓደኛዋ ሆንኩ››
ትላለች፡፡ በተጨማሪም ከሯሳ አልፋ ከሌሎች መሰል ቱሪስት ግብረሰዶማውያን ጋር እንድትፈፅም እንደምታደርጋት ትናገራለች፡፡
የአቶ እሱባለው ጥናት ካካተታቸው ግብረሰዶማያን 60 በመቶው በልጅነታቸው በመደፈራቸው ወደዚህ
ሕይወት እንደገቡ ነው፡፡ መደፈር ከሚያስከትለው የስነልቦና የሞራልና የመንፈስ ስብራት ማገገም ከባድ ስለሚሆን ታዳጊዎቹ በዚህ ሕይወት
ይቀጥላሉ፡፡ በድብቅም ከደፋሪዎቻቸው አልፈው ከሌሎች መሰል ሰዎች ጋር ወሲብ በመፈጸም ይገፉበታል፡፡ መደፈር ጣጣው ከባድ ነውና
ግብረሰዶማያን ድርጊቱን እንደ አንድ የማስፋፊያው ትልቅ መግነጢሳዊ ሃይል ይቆጥሩታል፡፡ በእነርሱ አጠራርም ‹‹ መከተብ›› ይሉታል፡፡ እንግዲህ አንድ ሕጻን ወይም አዋቂ «ከተከተበ» ከዛ ሕይወት መውጣት ይከብደዋል፡፡
ይህም ሞራሉን፣ተስፋውንና፣ለራሱ ያለውን ግምት ሲለሚያበላሽ ነው፡፡
አብዛኞቹ የሚደፈሩበት የዕድሜ ክልል ከ4 እስከ 16 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ
ሕፃናት ናቸው፤ይህም በጥናቱ ላይ ተገልጿል፡፡ ወደዚህ ሕይወት የገቡ ሕጻናት በዚሁ ተግባር ይቀጥላሉ ምክንያቱም ደፋሪው ግለሰብ
በድብቅም ቢሆን ለረጅም ጊዜ የወሲብ ጓደኛ አድርጎ ይዟቸው ስለሚቀጥል ነው፡፡ ፈታኙ ችግርም እዚህ ላይ ያርፋል ወላጆች ልጆቻቸው
መደፈራቸውን ባለማወቃቸው ልጆቻቸው በተሳሳተ ሕይወት ውስጥ ሲቀጥሉና ኋላ ላይ ይፋ የሚያደርጉት ማንነታቸው ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች
መጥፊያ ይሆናል፡፡
ሌላው መንስዔ አንዳንድ ወንድ
ህጻናትና ሴቶችም ጭምር ግብረ ሰዶም የሚሆኑበት መንገድ ነው፡፡ በተለያዩ ነገሮች በመታለል ለመጀመሪያ ጊዜም ቢሆን በእሺታ ድርጊቱን
ከፈጸሙ በኋላ ትልቅ የስነልበና ቀውስ ውስጥ የሚገቡ ታዳጊዎች መኖራቸው ነው፡፡ አማራጭ ስለሚያጡም ችግራቸውን ለቤተሰብ ከማሳወቅ
በዛው ህይወት ይቀጥላሉ፡፡ በአቶ እሱባለው ጥናት ላይ ስሙ ያልተጠቀሰ ሌላ ግብረሰዶማዊ ‹‹በ1993 ዓም በአምስት ዓመቴ አምስት
ብር ተከፍሎኝ በመታለል ነበር የተደፈርኩት፤ድርጊቱ ስላሳፈረኝና አማራጭ ስላጣሁ ለቤተሰብ ከመናገር ዝምታን መረጥኩ ሆኖም ከደፈረኝ
ግለሰብ ጋር ለ10 ዓመት ያህል ቀጠልን›› ብሏል፡፡ የመደፈር አደጋው በስፋት በሰፈር፣በትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን፣ በጎረቤቶቻቸውና
ዘመዶቻቸው እንዲሁም ባልታወቁ ግለሰቦች ተታለው በመወሰድ ወደዚህ ሕይወት እንደሚገቡ ጥናቱ በግልጽ ይጠቁማል፡፡
የሚደፈሩ ሕጻናት መብዛትም ሆነ ችግሩ እንዲስፋፋ ከፍተኛ ተሳትፎ ቱሪስቶችም እንዳሉና በቱሪዝም
በኩል ሌላኛው የግብረሰዶማውያን መግቢያ በር እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሕፃናትንም ለቱሪስቶች በማቅረብ የሚታወቁ የቱሪዝም ድርጅቶች
እንዳሉ ጥናቱ ያካተታቸው ግብረሰዶማውያን ይመሰክራሉ፡፡ሕጻናት ሲደፈሩ በቀላሉ መለየት ስለማይቻልም ችግሩ ለወላጆች ፈታኝ ይሆናል፡፡
ተመልካች ያጣው የግብረሰዶማውያን እንቅስቃሴም ታዳጊ ሕፃናትን ወደዚህ ህይወት በመክተት ላይ አተኩሮ ሥሩን በጠንካራ መሠረት ላይ
እየጣለ ይመስላል፡፡
ትምህርትቤቶች፤ዋነኞቹ የሰዶማውያን ኢላማ?
የግብረሰዶማውያን ጥቃት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በከፍተኛ
ሁኔታ የሚታጠቃው ህጻናትን መሆኑ እሙን ነው፡፡ሕጻናት ይህ ችግር በሰፊው የተጋረጠባቸው አደጋ ከቤታቸው አንስቶ እስከ አካባቢያቸውና
ትምህርት ቤቶቻቸው ይደርሳል፡፡
ትምህርት ቤቶች የተተኪው ትውልድ ማፍሪያ እንደመሆናቸው ሁሉ
የችግሩ ምንጭ የሚሆኑበትም አዳጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ዛሬ ላይ ወላጆች ልጆቻቸውን ውል ባግባቡ እማይረዱበት ሁኔታዎችም ይፈጠራሉ፡፡ትምህርት
ቤቶችም ሕፃናትንም ሆነ በእድሜ ከፍ ያሉ ታዳጊዎችን ከመሰል የወሲብ ጭቃቶች የሚታደጉበት መንገድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡በአንዳንድ
ትምህርት ቤቶችም በምን መልክ ተማሪዎቻቸውን እንደሚያነቁና እንደሚቆጣጠሩ በተለይም ችግሩ መስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ምን
እየሰሩ እንደሆነ ለማየት ሞክረናልም፡፡
አቶ ደርብ ወርቁ የአቡነ ጎርጎርዮስ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ
ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡እንደ እርሳቸው እምነት ትምህርት ቤቶች ብዙ መነቃቃት እንዳለባቸው ከወዲሁ ያሳስባሉ፡፡በትምህርት ቤታቸው
ያለውን ሁኔታ ሲያብራሩም «ለዚህ ችግር ብቻም ሳይሆን ለማንኛውም ማህበራዊ ቀወሶች በሕጻናት ላይ የሚያደርሰውን ችግር ለመቅፍ ትምህርትቤቱ
በጋይዳንስና ካውንስሊንግ ባለሞያ እየታገዘ ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ወላጆንና የሰርቪስ ሹፌሮች ሳይቀሩ ስልጠናና የማነቃቂያ ትምህርቶች
እንደሚሰጡ ይናገራሉ፡፡በተለይ ወላጆች የሚሳሠባቸውን
ርዕሰ ጉዳይ በገለፅ እያነሱ ይወያያሉ፡፡ የግብረሰዶማዊነት አደጋ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፈታኝ የስነልቦናም
ሆነ ማህበራዊ ቀውሶች በዚህ መልኩ አስቀድሞ ለመከላከል አመቺ አሰራር እንደሆነም ያምናሉ፡፡
በዚሁ ትምህርት ቤት ያገኘናቸው የጋይዳንስና ካውንስሊንግ
ክፍልሃላፊና የስነልቦና ባለሞያአቶምህረት
ሲሳይ እንደሚሉት ደግሞ ትምህርት ቤቶች ስጋቱ ኖረም አልኖረም ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ታዳጊዎችን
በጥብቅ ሁኔታ ሊረዱ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡እንደ እርሳቸው ልምድና በትምህርት ቤቱ ውስጥ ካላቸው ቆይታ ይህን መሰል አደገኛ የሆነ
ችግር አላጋጠማቸውም ነገርግን አላጋጠመንም ብለው እጃቸውን አጣጥፈው ቁጭ አላሉም እናም በሰፊው የምክር፣ትምህርትና ስልጠና ከሰባተኛ
ክፍል ጀምሮ ላሉ ታዳጊዎች እየሰጡ ይገኛል፡፡ከዚያ ክፍል በታች ያሉ ተማሪዎች ግንጉዳዩን ለመረዳት ስለሚከብዳቸው ወላጆችና መምህራኖቻቸው
እንዲያውቁት ከተደረገ በኋላ በሚመክሯቸውና በሚቆጣጠሯቸው መንገድ ላይ በማተኮር እንደሚሰሩ ይናገራሉ፡፡
ግብረሰዶማዊነትና ግብረሰዶማውያን በታዳጊ ተማሪዎች ላይ ሊያሳድሩ
ከሚችሉት ተጽዕኖም ሆነ አደጋ ልጆችን ለመጠበቅ እንደ ስነልቦና ባለሙያነታቸው ከማስተማርና ተማሪዎችን ከማንቃት ባለፈ የሚሰሩ ስራዎች
እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለጽም
«ይህ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው» በዋነኛነትምተማሪዎችን ከትምህርትቤት ባህሪያቸውና ድርጊታቸው
ጀምሮ በሚጓዙበት ሰርቪስ መኪና በቤታቸው ውስጥ የተለየ ነገር ማሳየት አለማሳየታቸውን የሚከታተሉበት ዘዴ ቀይሰው እንደሚሰሩ ይጠቁማሉ፡፡
ይህ የሚሰራውም ከወላጅ፣ መምህራን፣የተማሪዎች ሹፌሮች እና ከተማሪዎቹ ጋር በሚፈጠር ጠንካራ መስተጋብር ነው፡፡
ተማሪዎችንምን ዓይነትይዘት ያላቸው የስነምግባርም
ሆነ የስነልቦና ስልጠናዎች እንደሚሰጡ በጠየቅናቸው ወቅት ሲመልሱም፡፡ «በየጊዜው አዳዲስ ነገር የሚፈጠርበት አለም ላይ ነው ያለነውና
ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ እንተኩራለን፤ይህ ስልጠናና ምክር በአንድ ወቅት ብቻ አይሰጥም፤እንደተፈለገው በየወሩና አስፈላጊም ሲሆን
ተማሪዎችን በግል እየነጠልን ነው» ብለዋል፡፡
ከብዙ ተማሪዎች መካከል አንዱ በዚህ መልኩ ከተጠቃ ሌሎች ጔደኞቹን ይዞ ወደዚህ ሕይወት መግባቱ
አይቀርም እና ትምሕርት ቤቶች ፈተናቸው ከሌሎች የጠነከረ ነው። እንደ አቶ ምሕረት እምነትም አስቀድሞ ይህን ለመከላከል ጠቃሚው
ነገር ተማሪዎች ራሳቸው ግብረሰዶማዊ የሆነ ግለሰብ ወይም በግብረሰዶማውያን የተጠቃ ተማሪ ሊያሳይ የሚችለውን ባህሪ ለውጥ አስቀድመው
እንዲረዱ ማስተማርና ግንዛቤው እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። «ካለባበስ ጀምሮ፣ከሚከተሉት ስታይል፣ከሚፈልጉትም ነገር ቢሆን ተማሪዎች
በጥንቃቄ ተገንዝበው እኛ ጋር ሲመጡም እንዲህ አይነት ነገር አይተናል ብለው ጓደኞቻቸውንም እንዲታደጉ ማድረግ የሚችሉ ዜጎች እንዲሆኑ
ልንጥር ይገባል» ይላሉ።
ተማሪዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመደፈርና ወደዚህ ሕይወት የመግባት ዕድላቸው ሰፊ ነው
በእናንተስ ትምህርት ቤት ይህ ስጋት ምን ያህል ያሳስባችኋል ስንል ለጠየቅናቸው ጥያቄም ሲመልሱልን ‹‹ቀድሞ መዘጋጀት በራሱ ከስጋት
ነጻ ያደርግሃል፤ታዳጊዎቻችን የተጋረጠባቸውን ስጋት ነጻ ሆነው እንዲማሩ ማድረግ የምንችለውይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው፡፡››
ይላሉ፡፡
አይበለውና አንድ ተማሪ በዚህ መልኩ ቢደፈር የሚያሳየውንምልክት በመከተል እርዳታ የሚሰጠው
አካላዊ አደጋ እንደደረሰበትና እንዳልደረሰበት በነርስ ምርመራ ከተረጋገጠ ወደ ሃኪም እንዲወሰድ ከቤተሰብ ጋር በመመካከር ይሆናል።
በመቀጠልም ወሳኙና መሰረታዊው የስነልቦና ሕክምናምይሰጠዋል።በዚህም ብቻ አያበቃም ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ሆነ የማጣራት ሥራ ይጠበቅበታል
ምክንያቱም ይህን አደጋ ያደረሰው ግለሰብ ታድኖ ለፍርድ መቅረብ አለበትና ትምሀርት ቤቱ ከወላጅ ጋር በመተባበር ችግሩን ከምንጩ
ለማድረቅ ያልተቋረጠ ሥራ ይጠበቃል፡፡
«እኛ የግብረሰዶማውያንን ባህሪ፣ተግባር አለባበስና አመለካከት
ከዚህም ባለፈ አስከፊው ድርጊታቸውን ታዳጊዎቻችንን በሚመጥን መልኩ እናስተምራለን፤እንዲጠነቀቁም እናነቃቸዋለን» የሚሉት አቶምህረት
በግቢያቸው ውስጥ በዚህ ችግር የተጠቁ ሕጻናትና ታዳጊዎች ካሉ ለማወቅ የሚረዳቸው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያደርጉ ገለጹልን እኛም አያይዘን
ከሌላ ትምህርት ቤት የሚመጡ አዳዲስ ተማሪዎች እንደ ግብረሰዶማዊነት አይነት ችግር ይዘው ወደ እናንተ ቢመጡ በምን ታውቃላችሁ ስንል
ለጠየቅናቸው ጥያቄ ወደ ትምህርት ቤቱ የሚመጡ አዳዲስ ተማሪዎች ከቀላል ጀምሮ እስከ ከባድ የስነልቦና ፣ስነምግባርና ማህበራዊ ችግር
ይኑርባቸው አልያም አይኑርባቸው የሚያጣሩበት አሰራር እንዳለ ይናገራሉ፡፡ «በመሰረቱ ከሌላ ትምህርት ቤት ይህን መሰል አደገኛ ችግር
ይዘው የመምጣት ሰፊ እድል ስላለ አስቀድመን ማጣራት እናደርጋለን፣ ሌላው ቢቀር በትምህርትቤት እንኳን ወንድ ከወንድሴት ከሴት ተማሪዎች
ጋር ያላቸውን የቅርርብ ደረጃ እናውቃለን፡፡ወላጆችም ጭምር እንዲያውቁ እናደርጋለን፡፡ምክንያቱም ግብረሰዶማዊነት እጅግ በድብቅና
ሚስጢራዊ በሆነ መልኩ የሚደረግ ነገር ነውና» ይላሉ፡፡
ስለችግሩ በስፋት የሚያውቁ ታዳጊዎች እንዳሉ ሆነው አብዛኞቹ
ታዳጊዎች አዲስ ና አስደንጋጭ ይሆንባቸዋል፡፡እናም እነዚህን
ሕጻናት በማያሸብርና ትልቅ ጭንቀት ውስጥ በማይከት መልኩ ታዳጊዎች ሊረዱት፣ችግሩ ቢያጋጥማቸው ራሳቸውን
እንዴት እንደሚከላከሉና እንዴት እርዳታ እንደሚጠይቁም ሊሆን ግድ ይላል፡፡በዚህ ትምህርት ቤትም ተመሳሳይ ነገር እየተደረገ እንደሆነ
የጋይዳንስና ካውንስለሩ አቶምህረት ያስረዳሉ፡፡እንደ አቶምህረት ልምድም በትምህርትቤቱ ውስጥ እስካሁን ይህን አይነት ከባድ ችግር
እንዳላጋጠማቸው ይናገራሉ፡፡ከዚያ ይልቅ በስፋት የሚታየው የጉርምሥና
ወቅት የታዳጊዎች ሁሉ መሠረታዊ ችግር የሆኑት እንደ እና የፍቅር
ግንኙነቶች ናቸው ከ12 ዓመት በታች ባሉት ደግሞ ከወላጆች ጋር የተያያዘ እንደፍቺ ያሉ ቤተሰባዊ ችግሮች ናቸው፡፡
ችግሩን ሊከላከሉ ከሚችሉ ወገኖች መካከል መምህራን ዋነኞቹ
ናቸው፡፡በዚሁ የአቡነጎርጎርዮስ ትምህርትቤት መምህር በረከት
ይልማ እንዲህ ሲል ቃሉን ሰጠን፡፡ ‹‹በትምህርት ቤቶቻችን ቀለምን ብቻ ሳይሆን ስነምግባርን ጭምር
ልናስተምር ይገባል ምክንያቱም ግብረሰዶማዊነት እንደሃገር በጣም ያሰጋናል፤በተለይ ታዳጊዎቻችንን ያነጣጠረ በመሆኑ፡፡›› ይላል፡፡‹‹በኛም
ሆነ በሌሎች ትምህርት ቤቶች ስጋቱ አለ፤ምክንያቱም ተማሪዎቹ የህብረተሰቡ
አካል ስለሆኑ ነው፡፡ነገር ግን በኛ ትምህርት ቤት ውስጥ ፈፅሞ ይህ ችግር እንደሌለ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡›› ይላሉ ዛሬ ላይ
ያለው ጥንቃቄና አስተምህሮ ነገ ላይ ግን እንደማይከሰት ዋስትና ሊሆን እንደማይችልም ጨምሮ በማስረዳት እንደ መምህር ያየውን እውነታ
ያስቀምጣል፡፡
እንደ መምህር ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፤ይህ ማለት ደግሞ በከተማው ውስጥ ስላለው ሁኔታ መረጃ መምህራኖች ሊኖራቸው ይገባል፡፡የግብረሰዶማውያንን
አላማ፣እንቅስቃሴና የሚፈጥሩትን ችግርና ያላቸው ተጽዕኖ አስቀድሞ በመረዳት ተማሪዎቻቸውን መምከር ብቻም ሳይሆን ስብዕናቸውን መቅረፅ
ይችላሉ፡፡ይበልጥ ደግሞመምህራን ተማሪዎቻቸው ላይ ማሳደር ከሚችሉት የስብዕና ተጽዕኖ አንፃር ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ይገልፃል፡፡
መምህርንም ይህን ጉዳይ በተመለከተ ተማሪዎች ምን ያህል ጠይቀውህ
ያውቃሉ ስንል ላነሳንለት ጥያቄ ‹‹በእርግጥ ተማሪዎች ለማወቅ ካላችው ጉጉት የተነሳ ከተለያዩ መረጃ ምንጮች ያነበቡትንም ሆነ ያዩትን
ይጠይቃሉ፤የውይይት ሃሳብም የሚመጣው ተማሪዎች በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች በመነሳት ነው እናም እንደየእድሜያቸው ደረጃም ባነሱት
ማንኛውም ጉዳይ ላይ እናወያያቸዋለን›› ይላል እንደተጨማሪ ሃሳብም ይህ ችግር በመምህራንም ላይ እንዳይከሰቱ ብዙ ስራዎች እንደሚሰሩ
ጠቅሶ ሃሳቡን ያጠቃልላል፡፡
ከዚህበተጨማሪም ተማሪዎች በትምህርት ቤትም ሆነ ከትምህርት
ቤት ውጭ ጓደኞቻቸውን በደንብ ሊለዩ ይገባል፡፡ምክንያቱም እነዚህ ጓደኞቻቸው ራሳቸውን ሰውረው የዚያ ችግር ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ
አልያም የዚያ ድርጊት ቀጥታ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል መምህር በረከት ያስረዳል፡፡ ‹‹አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደቀልድ ሳይታሰብ
ይጀመራል›› ይላል መምህር በረከት በምሳሌ ሲያስረዳም በከረንቡላ ቤቶች ውስጥ አብሮ ከመዋል ከመነካካትና ጥልቅ ወደሆነ መቀራረብ
ይፈጠርና ታዳጊዎች በባህላችንም ሆነ በሐይማኖቶቻችን ፀያፍ የሆነውን ነገር ከሌሎች ጓደኞቻቸው ይወርሳሉ ይላል፡፡
መምህርት ቢታንያ ደምሴ ትባላለች፡፡ እንደመምህር ብቻም ሳይሆን
እርሷን መሰል ወላጆች ስጋት እንደፈጥረባቸው ትናገራለች፡፡ በተለይ ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እጅግ ውስብስብና ወላጆች የማይፈቱት
አይነት የሚሆንበት ጊዜያት ብዙ እንደሆኑ፤ በተለይ ደግሞ የግብረሰዶማውያን ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩና ተማሪዎቻችን ውለው እስኪገቡ
እንኳን ትልቅ ሃሳብ እንድሆነ ትገልጻለች፡፡
ወላጆች የልጆቻቸውን ውሎ ብቻም ሳይሆን ባህሪዎቻቸውንም በየጊዜው
ሊቆጣጠሩ እንደሚገባ ታሳስባለች ምክንያቱም በችግሩ ውስጥ ሆነው እንኳን ችግራቸውን በውስጣቸው እንደያዙ ወላጆች ለመረዳት በሚከብዳቸው
መልኩ ልጆች በአዲስ ማንነት ውስጥ ሊያድጉ እንደሚችሉ ከልምዷ ተነስታ ትናገራለች፡፡ የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ይህች መምህርት
የወላጆችን ስጋት ለመቅረፍ ትምህርት ቤትና ወላጆች ብቻ ምንም መፍትሄ እንደማያመጡ ታማነለች ይበልጥ ደግሞ የህግና ስርዓት እንዲሁም
ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጣልቃ ገብተው «ከስጋታችን ነፃ የምንሆንበት መንገድ ሊኖር ይገባል» ትላለች፡፡
ግብረሰዶማውያን ትኩረታቸውን በተማሪዎች ላይ ስለማድረጋቸው
ማረጋገጫ የሚሆነን በዜናአውታሮችም ሆነ አልፎ አልፎም በስማበለው ከተነገረን ወሬተነስተን ብቻ አይደለም፡፡በእርግጥም ተማሪዎች አደጋው
ከተጋረጠባቸው መቼም መጠቃታቸው አይቀርምና መጠንቀቁ ይበጃል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የዚያን ያህል መደፈራቸውን እንኳን በቅጡ ሳናውቅ
አድገው እነሱም ተመሳሳይ ችግር ሲፈጥሩ መስማት ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡በእርግጥ ትምህርት ቤቶች የነዚህ ግለሰቦች የወሲብ ምንጮች
ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ትምህርት ቤቶችም ይህን ሳይዘነጉ የራሳቸውን ጥንቃቄና መከላከያ መንገድ ሊያበጁ ይገባል፣ ወላጆችም በሰቀቀን ከሚያሳልፏት
የዕለት ውሎ በነፃ አእምሮስራቸውን አከናውነው ወደቤታቸው ሲመለሱ ደስተኛና ጤነኛ ልጅ እንዲጠብቃቸው መመኝት ብቻ ሳይሆን በተግባር
አንድ ነገር ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ትውልዱ ‹‹እየተከተበ›› ነው
አንድን ማህበረሰብ ከሌላው ከሚለዩት ነገሮች ውስጥ ቋንቋ፣ባህል ወይም አለባበስ ሊሆን ይችላል፡፡
በተለምዶ በከተማችን የአራዳ ቋንቋ ወይም ቀበሌኛ የምንለው ቋንቋ ጋር ተመሳሳይነትና ተወራራሽነት ያለው ብዙ ቃላቶችና አገላለጾች
በግብረሰዶማውያን ዘንድ መኖሩን ደግሞ አቶ እሱባለው ይጠቅሳሉ፡፡
ግብረሰዶማውያን ራሳቸውን ‹‹ዜጋ›› እያሉ ይጠራሉ፡፡ ትርጓሜውም ‹‹የኛ›› ወይም ‹‹የግብረሰዶማውያን
ወገን›› የሚል አንድምታ አለው፡፡ በከተማና በገጠር ያለውን ማህበረሰብ የሚለዩበት ቃላቶችም አሏቸው፡፡ከገጠር የሚመጡ ወጣት ወንዶችን
‹‹ቆምጬ›› ብለው ሲጠሩ ከተሜውን ደግሞ ‹‹ዞላ›› በማለት ይለያሉ፡፡
በመሃከላቸው በሚኖር የግንኙነትና የወሲብ ሚናም የሚሰጡት ስያሜም አላቸው፡፡ ‹‹አውጪ›› ማለት
ወሲብ ፈጻሚ ወንድ ሲሆን ወሲብ የሚፈፀምበት ወንድ ደግሞ ‹‹ወጪ›› በማለት ይጠሩታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜም ሰዶማውያኑ በዚህ ሚናቸው
ይቀጥላሉ፡፡ ተመሳሳይ በሆነ መልኩም ‹‹ከታ›› እና ‹‹ከላ›› የሚሉት ድርጊትም አለ፡፡‹‹ ወሲብን ከላይ ሆኖ የሚፈፅም ‹‹ከታ
ሲሉት ወሲብን ከስር ሆኖ የሚፈፅም ሰዶማዊ ደግሞ ‹‹ከላ›› ይሉታል፡፡ ይህን መሰል የሚስጢር ቃላት በቀላሉ ለመግባባት ይጠቀሙበታል፡፡
በወንዶቹም ብቻ ሳይሆን ሴት ግብሰዶማያንም የራሳቸው መጠሪያ አላቸው፡፡ በግንኙነት ውስጥ የወንድን
ሚና የምትይዝ ሴት ግብረሰዶማዊ ‹‹ከቤ›› ስትባል የሴትነትን ቦታ የምትሸፍነው ‹‹ለታ›› ይሏታል፡፡
በእነዚህ ግብረሰዶማውያን ዘንድ በስፋት የሚታወቀውና የመስፋፋታቸውን ትልቅ ምስጢር የሚገልጹበት
ቃል ቢኖር ‹‹ መከተብ›› ነው፡፡ መከተብ አንድን ታዳጊ ወይም አዋቂ አስገድደውም ሆነ አታለው በመድፈር የነሱ አባል ሲያደርጉ
ድርጊቱን ‹‹መከተብ›› ብለው ይጠሩታል፡፡ መከተብ አደገኛ ጦስ እንዳለውና አንድ ሰው ከተከተበ ሞራሉ፣መንፈሱ ስለሚሰበር እና ተስፋ
ስለሚቆርጥ ከጉዳቱ ከማገገም በዚህ ሕይወት መቀጠሉን ይመርጣል፡፡ይበልጥ ደግሞ ይህ ድርጊታቸው እንደማሰሪያና ማላመጂያ ይጠቀሙበታል፡፡
ትውልዱን እንዲህ እያደረጉ በወጥመዳቸው እየጠለፉና እየከተቡት የሚገኙ ግብረሰዶማውያን ቃላት
ብቻ ሳይሆን አለባበሳቸውም መለያቸው ነው፡፡ በከተማችን የሚታየውም የተለመደ አለባበስ በመሃከላችን እንደልባቸው ሳለዩ እንዲቀጥሉ
የረዳቸውም ይመስላል፡፡ ባለማወቅም ተመሳሳይ አለባበሶችን እንለብሳለን፡፡ ይህንንም አቶ እሱባለው ጥናት ያደረጉባቸው ግብረሰዶማያን
ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ የከተማ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ባላማስተዋል የሰዶማውያንን አለባበስ ያዘወትራሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም ‹‹አውጪ››
የሆነው ሰዶማዊ በግራ ጆሮው ሎቲ ያስራል፡፡ ‹‹ወጪ›› የሆነው ደግሞ ጠባብና በተለምዶ ‹‹ቀሪያ›› ወይም ‹‹ስኪኒ›› የሚባለውን
ሱሪ ያዘወትራል፡፡ሰፊ ሱሪና ሰፊ ቲሸርት ያደርጋል፡፡ሌላኛው መለያቸውም ትኩረት ለመሳብ ብዙ አይነት ደማቅና ብርቅርቅ ቀለማት የበዛበት
ልብስ ይለብሳሉ፡፡ በእጅ ላይ የሚታሰሩ ብዙ አይነት ጌጣጌጦችንም ያደርጋሉ፡፡ የዚህ አላማም ትኩረትን ለመሳብ የሚደረግ እንደሆነ
ብዙዎቹ ግብረሰዶማውያን ይናገራሉ፡፡
በሴቶቹ በኩልም ከፍታ ያለው ጫማና ትኩረት የሚስቡ የልብስ ቀለማት ያዘወትራሉ፡፡እጅግ ሰፋፊና
ጎልተው የሚታዩ ነጫጭ ቀበቶዎችን ያደርጋሉ፡፡ ጦቶቻቸውን አጉልተው የሚያሳዩ የጡት ማስያዣዎችን የደማቅ ቀለማት ውጤት በሆኑ ጉርድ
ቲሸርቶች ይደርባሉ፡፡
«ሕግ ሃይ ሊለው ይገባል»
ችግሩ ስሩን እየተከለ ሲመጣ አብዛኞቻችን የአትዮጵያ የቤተሰብ ህግ ምን ይላል ብለን መጠየቃችን
ግድ ይላል፡፡ይበልጥ ደግሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህጋችን ምን አይነት ቅጣት እንደሚያስቀምጥ መጠየቃችንም አይቀርም፡፡ እኛም ወደ አዲሰ
አበባ ዪኒቨርሲቲ በማምራት መምህር፣ የህግና አስተዳደር ትምህርቶች
ኮሌጅ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ተባባሪ ዲንና በሰብአዊ መብቶች ጥናት እየሰሩ ያሉ ባለሙያ አነጋገርን፡፡ አቶ ሲሳይ መንግስቴ ይባላሉ፡፡
አቶ ሲሳይ እንደጠቆሙንም የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ በዋነኛነት በወንድና
በሴት መካከል መሆን እንዳለበት ነው እውቅና የሚሰጠው በህግመንግስቱም እንደ መርህ ይህ ነው የተቀመጠው፡፡ የፌደራል ህግ በተለይም
በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ብቻ የሚሰራ አለ፣የክልል መንግስታትም የየራሰቸው የሆነ የቤተሰብ ህግ አውጥተዋል፡፡ እነዚህ ህጎች በባህልም
ሆነ በሃይማኖት እንደሁም በማህበረሰባችን አመለካከት እይታ ጋብቻ በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ብቻ መሆን እንዳለበት ይደነግጋሉ፡፡
ህጉ
ስለተመሳሳይ ፆታ ምንም የሚለው ነገር እስከሌለ የተመሳሳይ ጋብቻ ህገወጥ ነው ብሎ ለመደምደም አያስቸግርም ይሆን ብለን ላነሳነው
ጥያቄ አቶ ሲሳይ ሲያብራሩልንም፤ ከሲቪልና ፍትሃ ብሄራዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ተያይዞ በህግ ያልተከለከለ ነገር እንደተፈቀነ ይቆጠራል
የሚል ነገር አለ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ የጋራ መግባባት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ ምክር ቤት የቤተሰብ ህግ ሲያወጣ አንድ ወንድ ካንድ ሴት
በላይ ሊያገባ እንዲችል ይፈቅድ ነበር ይህም በተለይ በእስልምና ሃይማኖት ከታዮች በሆኑ በክልሉ ህዝብ ዘንድ ያለውን ሁኔታ በማሰብ
ቢሆንም ቆየት ብሎ የመጣው የሴቶች ተቃውሞና ከፌደራል ህገመንግስቱ ጋር ይጋጫል የሚል አቋም እየጠነከረ ሲመጣ የቤተሰብ ህጉ ተሻሽሏል፡፡
በቤተሰብ
ህጉ በወንድና በሴት መካከል ብቻ ስለሚልም አስራሩ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ሌላ ዓይነት ጋብቻን አያካትትም ማለት ነው፤ካላካተ ደግሞ
ወንጀል ነው፡፡ በ1997ዓ.ም ስራ ላይ የዋለው አዲሱ የወንጀል ህግም ይህን ድርጊት ወንጀል አድርጎ ገልፆታል፡፡ ይህ ማለትም ከአንድ
ወንድና ከአንዲት ሴት ውጭ ጋብቻ ክልክል እንደሆነና በወንጀልም የሚታስቀጣ እንደሆነ ያትታል፡፡ ባገራችን ያለውን የወንጀል ህግ
ስንመለከትም ክልከላ በተዘዋዋሪም ቢሆን ያደረገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እንደ ወንጀል ከሚከለክላቸው ነገሮች ግብረሰዶም አንዱ ነው፡፡ እንደወንጀል ድርጊት ስልተፈረጀም ያስቀጣል፡፡
ከኢትዮጵያ
የህግ ስርዓት አንፃር በግልፅ አልተከለከለም ብለን ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ ከህግ አንፃርም ያሉትን ህጎችና አሰራሮች ከተጠቀምን የተለየ
ህግ፣ የተለየ ፖሊሲ ማውጣት አስፈላጊ እንዳልሆ የአቶ ሲሳይ እምነት ነው፡፡ ያሉትን የህግን፣የባህልን ፣የሃይማኖትን እሴቶች ለመጠበቅ
ያለው የህግ ስርዓት በቂ ነው፡፡ በተለይ ከሰብዓዊ መብት አያይዘው ጥያቄ ሚያነሱ አግባብ ያለው ምላሽ ይሰጣል፡፡
በበለፀጉት ሀገራት የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብዓዊ መብት ያለገደብ መከብር አለበት
የሚል አመለካከቴ አለ፡፡ ይህኛውንም ድርጊት እንደሰብአዊ መብት ተደርጎ መቆጥር አለበት ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ አንድ ሰው በፈለገው
መልክ ትዳር ሊፈፅምና በግል ስሜቱ ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለብን፥ ማንኛውንም ድርጊት ያስደስተኛል፣ይጠቅመኛል ብሎ ካደረገው
ምንም ችግር የለውም የሚል አስተሳሰብም አላቸው፡፡ ይህ በምህራባውያን ዘንድ የምናያቸው የሚዲያ ተጽዕኖዎች በዚህ መልኩ ስለሚንፀባረቁ
ህጋችን ይህን ሁኔታ በሚከላከልበት መልኩ ሊሆንም ይገባል፡፡
አስከፊው እውነታ፤ አካላዊና ስነልቦናዊ ቀውሶቹ
አብዱልገፋር ሸሪፍ ይባላሉ፡፡
በስነልቦና ትምህርት የድህረ ምረቃ ተምረው ፣በጥናትና ምርምር ላይ ለአራት አመታት ቆተው በተለያዩ የግል ኮሌጆች የስነልቦና መምህር
ሆነው አገልግለዋል በአሁን ወቅት ደግሞ በአፍሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያ «ቤታችን» በተሰኘ ፕሮግራም የስነልቦና ምክሮችን ያቀርባሉ፡፡
በተለያዩ ት/ቤቶች እየዞሩም ለቤተሰቦችና ለሕጻናት የስነልቦና ስልጠናዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
ካለን ባህል አንጻር በተለይ በወላጆችና በሕጻናት መካከል በግልጽ አይወራም፡፡ ወይም ውይይት
ያን ያህል የተለመደ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በምን መልኩ ነው፡፡ መነጋገር እንደሚችሉ ስንጠይቃቸውም‹‹እንደኢትዮጵያዊ
ሆነህ ንገረኝ ካልክ እስከምን ድረስ ነው ልጆችን ግልጽ ሆነን ማውራት ያለብን? ቆጥበን ማውራት ይኖርብን አይኖርብን በባለሙያዎች
ዘንድ ራሱ ክርክር የሆነ አጀንዳ ነው፡፡በጣም ግልጽ እንሁን የሚሉም አሉ፡፡›› ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን የልጆችን የመረዳት አቅም ከግምት
ወስጥ ማስገባት እንዳለብን ያሳስባሉ፡፡በዚህ መሰረትም በእድሜ ደረጃም እስከ 7 ዓመት ያሉ ታዳጊዎች፣ እስከ13 ወይም 16 እያልን
ልንለያቸው እንችላለን፡፡
የወላጆች ልምድ የዳበረ ቢሆን ልጆችን በነዚህ እድሜ ላይ መጥኖ መንገር ይችሉ ይሆናል፡፡ መገናኛ
ብዙሃንም ይህን ማስተማር አለባቸው፡፡ የወላጆች ሃላፊነትም በመጠየቅና በመረዳት ላይ የተመረኮዘ መሆን ይኖርበታል፡፡ እንኳን ግብረሰዶሶም
ይቅርና እኔ ከየት ተፈጠርኩ፣ እንዴት ወለድሽኝ በማለት በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ የመራቢያ አካላቶቻችን አፈጣጠርና ተግባር
በደንብ አይገነዘቡም፡፡ በህጻናት ደረጃም ቆሻሻን ለማስወገድ እንደሚረዳን አድርጎ ማስረዳት ብቻ በቂ እንደሆነም የአቶ አብዱል ገፋር
እምነት ነው፡፡
ይህ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ በጣም ብዙ ችግር ይደርሳል፡፡ የመራቢያ አካላቶቻችን ሌላ ስያሜ
እየሰጠናቸው ሕጻናት ግራ መጋባት ውስጥ መግባት እሚደርሱበት ሁኔታም አለ፡፡ ያም ሆነ ይህ ያደግንበት ባህል በቂ ስላልሆነ ወላጆች
ብዙ ነገሮችን ታሳቢ አድርገውና የልጆቻቸውን ባህሪ የማወቅ ጉጉት በሚመጥን መልኩ በጥንቃቄ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡
«እናም በተጨባጭ ይህ ችግር ለልጁ የሚያሰጋው ከሆነ ግን እንግዲህ ወላጆች ይህን አይነት ድርጊት እንዳለና ልጁ ሊጠነቀቅ እንደሚገባው
ሕጻኑን በሚመጥን ልኬት ልናስረዳው ይገባል»ይላሉ፡፡
ልጆች ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ ወስብስብ ፅንሰሃሳብ (Abstract Concept) መረዳት ይጀምራሉ፡፡
ለምሳሌም ፍቅር የምንለው ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ እየጨመርን
ማስረዳት እንችላለን፡፡ እስከ 11 ዓመትምብዙ መሠረታዊ ነገሮችን እየተረዱ ይመጣሉ፡፡ ከዛ በኋላም በአንጎላቸው ብዙ ለውጦች ይካሔዳሉ፡፡ የሚሟሉ ነገሮችም አሉ፡፡ በመሠረቱ ሳይንስ 75 በመቶ
የጭንቅላት እድገት አምስት ዓመት ላይ ያበቃል ይላል፡፡ ብዙ ነገሮችን መረዳት የሚጀምሩም በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ቢሆንም ውስብስብ
የሆኑ ነገሮችን ግን መረዳት አይችሉም፡፡ እነሱን በሂደት ብቻ ነው የሚረዱት፡፡
እድሜያቸው እየጨመረ በመጣ ጊዜ ጠንካራ ሃሳቦችን የመረዳት አቅማቸውም እኩል እየጨመረ ይመጣል፡፡ ግልጽነታችን ግን ጥንቃቄ እና ጨዋነትን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት ወላጆች
ይህን ማድረግ እሳናቸው ከሆነና መፍትሔ ከፈለጉ የስነልቦና ፕሮግራሞችን መከታተልና መጽሐፍትን ማንበብ ግድ ይላቸዋል፡፡
አንድ የቤተሰብ አባል በተለይ ሕጻን በዚህ ችግር የተጠቃ መሆኑ የምንለይበት ምልክት መኖር
አለመኖሩን አቶ አብዱልገፋርን በጠየቅናቸው ወቅት ‹‹ድርጊቱን ጠቅልለን እንድናየው ያስገድደናል›› ይላሉ የወሲብ ጥቃት(Sexual
abuse) ሕጻናት ያለፍላጎታቸው ተታለውም ሆነ ተገደው ሰውነታቸው ለአካለ መጠን ባልደሰበት ሁኔታ ተገደው የሚያደርጉት ማለት ነው፡፡
ይህ የወሲብ ጥቃት በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ ሲፈፀም በጣም ውጤቶች አሉት፡፡ ይህን በተመለከተም እንዲህ ዘርዘር አድርገን አይተነዋል፡፡
በሕፃናት ላይ የወሲብ ጥቃት ከተካሔደ ምን ምልክት ሊታይባቸው
ይችላል?
1. አንደኛ ከተለመደው በላይ የሆነ የወሲብ እውቀት ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ የአምስት አመት
ልጅ የወሲብ እውቀቱን መገመት ይቻላል፡፡ ከዛ በላይ ሲረዳና ስለጉዳዩ ደጋግሞ ሲጠይቅ እንደ
አንድ ምልክት ልንወስደው እንችላለን፡፡
2. አካላዊ ጥቃት እንደተከሰተ በወቅቱ ደም መፍሰስ ሊታይ ይችላል፡፡ በሚፀዳዳበት ወቅትም
ሰገራው ደም ቀላቅሎ ሊወጣ ይችላል፡፡
3.ያልተለመደ ቁስለትና ማሳከክ በመቀመጫ አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ይታይበታል፡፡
4. ሕጻናት የመድፈር አደጋ ያደረሰባቸውን ግለሰብ በአቅራቢያቸው ካለ ይህን ግለሰብ ሲፈሩና
ሲሸሹ እናያለን፡፡ ምንም እንኳን ተጨባጭ መረጃ ባኖረንም ታዳጊዎች ይህን ጉዳት ያሰጨደረሰባቸውን ግለሰብ ሲያዩ በፍርሃት ሲያለቅሱ
እናያለን፡፡
5.እንቅልፍ ማጣት ቢተኙም እንኳን ሌሊት፥ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መባነንና መጮህ፡፡
6.የምግብ ፍላጎታቸው በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ፥ አልያም በተቃራኒው ምግብ በጣም ይመገባሉ ምክንያቱም ምግብን እንደ እልህ መወጫ አድርገው ሊቆጥሩት
ስለሚችሉ፡፡
7.ከ12 ዓመት በላይ በሆኑ ሕጻናት ላይ ደግሞ ለትምህርት ያላቸው ፌላጎት ሊቀንስ ይችላል፡፡
8. በከፍተኛ ሁኔታ ተቃራኒ ባህሪ ሊንጸባረቅባቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህልም በፍጥነት ቶሎ
ቶሎ የተደፈሩበት የሰውነት ክፍላቸውን አልያም ሌላም ቦታ ቢሆን ሊታጠቡ
ይችላሉ፡፡
9.በወሲብ ዙሪያ ከመጠን በላይ የሆነ ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ይህ በስፋት የሚሆነው እድሜያቸው
ከፍ ባሉ ታዳጊዎች ነው፡፡
10. ባልተለመደ መልኩ አይነምድራቸውን መቆጣጠር ያቅታቸውና በሱሪያቸው ላይ ሊለቁት ይችላሉ፡፡
11. በእድሜያቸው ከፍ ያሉ ታዳጊዎች ከቤት መጥፋት ወይም ጠንከር ሲል ራሳቸውን ለማጥፋት
ይመክራሉ፡፡
12. በማንኛውም ጉዳይ ራሳቸውን ወንጀለኛ ያደርጋሉ፡፡
ሁሉም ወላጅ ልበ ሊለው የሚገባ ነገር ቢኖር እነዚህ መጠቆሚያ ነጥቦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት
ልጆቻችንን ልንከታተል እንደመቻላችን ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተመሳሳይ ምልክቶች የሌላ ችግር መንስዔ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጥንቃቄም
ልናደርግ ይገባናል፡፡ አንዱን ምልክት አገኘን ማለት ልንደመድም
ይገባል ማለት አይደለም፡፡
ወላጆች ምን ያድርጉ?
ወላጆች በምን አይነት ሁኔታ ችግሩን ማስታመም ይችላሉ? ወይም ልጆቻቸውን መርዳት ይችላሉ የሚለው
ጥያቄ የብዙዎቹ ወላጆች ስራ ምታት ነው
‹‹ወደ እርዳታው ከመግባታችን በፊት መከላከያው ላይ ብናተኩር ይገባል›› ይላሉ፡፡ ሳይቃጠል
በቅጠል እንዲሉ በመከላከል ብናደርገው ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም እንደእርሳቸው ቀደምት የዳሰሳ ጥናት ሆነ የሌሎች ባለሙያዎች ጥናቶች
እንደሚያሳዩት አብዛኛው ቅርብ ዘመዶቻቸው፣በሰራተኛ፣በቤት ዘበኞች፣በእንግዶች፣ በእንጀራ አባት፣ በአጥኚ አስተማሪና በሃይማኖት አስተማሪዎች
ወንዶች ሕፃናት የመደፈር አደጋ ይደርስባቸዋል፡፡
ወላጆች ወደቤት ለመጣ እንግዳም ባቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቻቸው አደራ ሰጥተው ባይሄዱ ጥሩ ነው፡፡
ልጆቻችንም ደህንነት ስንል በመጠኑም ተጠራጣሪ ብንሆን ክፋት የለውም፡፡ ልጆቻቸውን ከጎረቤቶቻችን ጋር ለረጅም አመታት በሰላምና
በፍቅር ቆይተው አንድ ቀንም ብትሆን ይህች አደጋ ልትደርስባቸው ትችላለችና፡፡
ግብረደሶማዊነት በለምድ የሚዳብር ባህሪ በሳይንስ አጠራሩ (Learned Behavior) ይባላል፡፡
ይህም ማለት በተፈጥሮው ግብረ ሰዶማዊ ሆኖ የሚፈጠር የለም ነገር ግን በልምድና ከሕይወት በምንወስደው ትምህርት ወደዚህ እንገባለን፡፡
ምንም እንኳ ግብረ ሰዶማውያን በተፈጥሮ ያመጡት እንደሆነ አድርገው ቢከራከሩም፡፡
በዚህ ደረጃ ወላጅ የጠረጠራቸው ታዳጊዎች ካሉት መጀመርያ ወደ ህክምና ይወሰዳሉ፡፡ አካላዊ
ጉዳት የሚያደርስ ድርጊት በመሆኑም ነው፡፡ እነዚህ አካላዊ ጉዳቶች የፊንጢጣ መገልበጥ፣ መድማት፣ ኢንፌክሽንና ዙሪያው ላይ መላላጥና
የአባላዘር በሽታ ያመጣል፡፡ ከተፈጥሮ ህግጋት ውጭ በመሆኑም መድሃኒት እንኳን ሲወስዱ ምን ያህል እናውቃለን፡፡ ቦታው ከተሰራበት
ዓላማ ውጭ ስለሆነም እንዲያስተናግድ ሲሆን ከባድ አደጋ ይደርስበታል፡፡
ከዛ በሃላ ችግሩ እውነት ሆኖ ከተለየ በፍጥነት ወደ ስነልቦና ባለሞያ መውሰድ ይገባናል፡፡
የተደፈሩ
ሕፃናት ምን አይነት ባህሪ ያንፀባርቃሉ?
v
ያለምንም ምክንያት ይነጫነጫሉ፡፡ በጣም ነጭናጫ ሆነው እንዲያድጉ
ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ባህሪያቸውም ከ20 እና 30 ዓመት በሃላም ሊታይ ይችላል፡፡ የትምህርት ፍላጎታቸው ሊሞት ይችላል፡፡
v
ተስፋ ቢስ ይሆናሉ፡፡ ለደረሰባቸው በደል ሃላፊነቱን በራሳቸው
ላይ ስለሚጭኑ ፀፀት፣ተስፋቢስነትና ቁጭት ውስጣቸውን ያብሰለስለዋል
v
የበታችነት ስሜት ያጠቃቸዋል፡፡
v
ጭንቀትና ድብርት ሁሉም ተጎጂዎች ላይ ይታያል ማለት ይቻላል፡፡
አንዳንዶቹ ግን ሊደብቁት ይሞክራሉ፡፡
v
ጥቃት ጥቃትን ይወልዳል እንዲሉ በዚህ መልኩ ጥቃት የደረሰባቸው
ታዳጊዎች በተራቸው ሌላውን ሰው ወደማጥቃት ይሔዳሉ፡፡
v
እስከዛሬ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም እነዚህ ታዳጊዎች
ውስጣቸው የታመቀ ቁጣ ይኖራል፡፡ ቶሎ ቱግ ሲሉና ቂም ሲይዙ ጉዳት በውስጣቸው እንዳለ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
v
ሰዎችን ሲበቀሉ እንኳን እየተበቀሉ መሆናቸው አይታወቃቸውም፡፡
v
ራሳቸውን በማጠር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሰው ልጅ ክብር፣ፍቅርና
ርህራሄ አይኖራቸውም፡፡
v
እድሜ በሚጨምሩበት ጊዜ ወንጀለኛ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሰፊ
ነው፡፡
ሕጻናት መናገር ባይችሉ እንኳን ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ አላቸው፡፡ ጥቃቱ በግልፅም
ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ውስጣቸው ይቀራል፡፡ «ተጠቅቻለሁ፣ሃይ ባይ የለኝም፣ ማንም የሚደፍረኝና ስሜቱን የሚያረካብኝ ፍጡር ነኝ
ሲሉ ራሳቸውን በሃዘን ይሞላሉ፡፡ ለተመሳሳይ በቀልም ይነሳሳሉ፡፡ ይህም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አይነት ችግር ይዞልን ይመጣል፡፡
ባህልንና ማንነትን መጠበቅ የህልውና ጉዳይ ብቻም ሳይሆን ዛሬ ላይ ጤናማ ሕብረተሰብ ይዞ የመኖርና
ያለመኖር ጥያቄ ነው፡፡ በመሆኑም መሰል አዲስ ችግር ወደሃገራችን አስገብተን እስኪስፋፋ በዝምታ ማየት የመጪ ትውልድ አጥፊ ያደርገናል፡፡
በግብረሰዶም የተነሳ ሊከሰት የሚችለውን ማሐበራዊና ኢኮኖሚያዊ ይበልጥ ደግሞ ተተኪ ትውልድ ማጣት አሳሳቢ ነውና ሁላችንም ዝምታውን
ልንሰብር ይገባል፡፡
Comments
Post a Comment